ዜና ፍልሰታ
ከመጽሐፈ
ልደታ የተቀዳ ታሪክ ነው
ፈላስያን ከሀገር
ወደ ሀገር ይዘዋት የሚሰደዱ ስንቃቸው፣ አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ በልቡ ትክሻ የተሸከማት ተስፋው ዛሬ ከሚያልፈው ወደማያልፈው
ከሚያረጀው ወደ ማያረጀው ሄደች፡፡
ከመሞቷ አስቀድሞ
ከሄዋን ጀምሮ ያሉ ቅዱሳት አንስት መጥተው እጅ ነሷት፤ እናቷ ሐና፣ ከዘመዶቿ ወገን የምትሆን ኤልሳቤጥም መምጣታቸውን ቅዱስ ጴጥሮስ
ተናግሯል፡፡ እነሱ መጥተው ሰላምታ እያቀረቡላት ሳሉ ከአዳም ጀምሮ ያሉ አበው እጅ ሊነሷት ሲመጡ ማየቱንም ቅዱስ ጴጥሮስ መስክሯል፡፡
ሁሉም አበው እጇን እግሯን እየሳሙ ተሳለሟት አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ ሁሉም ከጻድቃን ወገን የቀረ አልነበረም፡፡
ዳዊት በሚዘምረው
መዝሙር ቤቱ በጣዕመ ዝማሬ ተሞላ፤ ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሁለቱ ሊቃነ መላእክት የወርቅ ጥና ይዘው እንዲወርዱ አዘዘ፤
ንፁሕ ዕጣን እያገቡ እመቤታን ታማ የተኛችበትን አልጋ እየዞሩ ሲያጥኑ አካባቢውን በጎ መዓዛ አወደው፤ ከእነርሱም ጋራ አባቶቿ ነቢያት
ማዕጠንት ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ ከገነት እፀዋት አበቦችን ይዘው የመጡ መላእክትም ነበሩ
ለዚህ ክብር
የበቁባት ልጃቸው ወደ ሰማይ የምትወሰድበት ጊዜው አሁን ነውና ከአበው ማንም በሰማይ የቀረ የለም፤ ምድሩን ሰማይ፣ ሰማዩን ምድር
ያደረገችው በእመቤታችን ዕለተ ዕረፍት ማን በሰማይ ይቀራል፡፡ ከመወለዷ አስቀድሞ በትንቢት ደጅ ይጠኗት እንደነበረ ዛሬም ነፍሷን
ይዞ ልጇ በሚያሳርጋት ጊዜ እያመሰገኑ ሊቀበሏት ይጠባበቃሉ፡፡
በዐፀደ ነፍስ
ካሉ ቅዱሳን ጀምሮ በዐፀደ ሥጋ እስካሉ ሐዋርያት ድረስ ከበዋት እንደቆሙ ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወረደ፤ ከአጠገቧም
ቆሞ ሰላምታን ከሰጣት በኋላ ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ ተቀበላት፡፡
ነፍስን የነሳላት ነፍሷን በእቅፉ አድርጎ ሳማት፤ ያቀፈችው ጌታ አቀፋት፤ የሳመችው
ልጇ ሳማት፤ በዙሪያዋ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ደስ አላቸው፤ መላእክትም አመሰገኑ፤ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤
ንግሥቲቱ የወርቅ ልብስ ለብሳ በቀኝህ ትቆማለች›› የሚለውን መዝሙሩን ሲዘምር ቅዱሳን ሁሉ አብረውት አመሰገኑ፡፡ በቅዱሳን ዘንድ
ነፍስ ወደ ፈጣሪዋ ስትመለስ የሚሰማው ምስጋና እጅግ ታላቅ ነው በዚህ ዓለም መወለዳችን ምጥ የሚያስረሳ ደስታን ያመጣል በወዲያኘውም
ዓለም መንግሥተ ሰማያትን መውረሳችን በዓለም የደረሰብንን መከራ ሁሉ የሚያስረሳ ደስታን ስለ ሚያመጣ ቅዱሳን ሁሉ እልልታን ያሰማሉ
እመቤታችንም ነፍሷ ከሥጋዋ ስትወጣ እልልታው የደመቀ ነበረ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ
ዐይኖቿን ከደናቸው ጴጥሮስና ጳውሎስ ደግሞ እጆቿን እግሮቿን አስተካከሉ፡፡ የለበሰችውን ልብሷን ግን ማውለቅ አልቻሉም፤ በሰማያዊ
ብርሃን ሰውነቷ ተሞልቷልና ከዚያ በኋላ ልብሷን መንካት አልቻሉም፡፡ ይህ ታሪክ ጥር 21 የተፈጸመ ነው የእመቤታችንም ፍልሰት ያንጊዜ
ነው፡፡ የሰሞኑን ታሪክ ደግሞ በቀጣይ እንመጣበታለን ፡፡
No comments:
Post a Comment