>

Saturday, 28 September 2019


መስቀል በኢትዮጵያ
እግዚአብሔር ለሕሙማን የሚቀባውን ዐጽቀ በለስ በኢትዮጵያ እጅ እንዳስቀመጠው መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ ያንጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ተማርከው ፋርስ ባቢሎን ሲወርዱ፤ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ናቡከደነፆር ሲሠለጥንባቸው እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለአሕዛብ ከመገዛት ጠበቃት፤ የጽዮንን ልጆች ያገኛቸው መከራ በኢትዮጵያ ላይ አልደረሰባትም፤ ነቢዩ ኤርምያስ የመከራው ቀን እየደረሰ እየደረሰ ሲመጣ ሞትም በእስራኤል ፊት ጥላውን ሲያጠላ የኢትዮጵያ ነገር እጅግ አሳስቦታል  ‹‹ይህን ኢትዮጵያዊ ምን ላድርገው›› ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ እግዚአብሔርም ለድውያን የሚሆነውን ፈውስ ቆርጦ በሙዳዩ ይዞ እንዲመጣ እዘዘው አለው፤ ኢትዮጵያዊው ሰው እንደታዘዘ ቆርጦ በሙዳይ የጨመረውን መድኃኒት ይዞ ሲመለስ ከመከራ ለመዳን የተዘጋጀለትን እንቅልፍ ለስድሳ ስድስት ዘመናት አንቀላፋ፡፡
ይህ የፈውስ ዛፍ ሕሙማን የተፈወሱበት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው፤ ኢትዮጵያዊው ሰው ከሕሙማኑ ሳያደርሰው ለላከው ነቢይ ለኤርምያስም ሳይሰጠው መቅረቱ ለምን ይመስልሃል? ዘመኑ ገና መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ነገር ግን ቢያንቀላፋም በእጁ ያለውን የፈውስ እንጨት በዓለም ያሉ ሕሙማን ሁሉ በተስፋ የሚጠብቁት ስለሆነ አልጣለውም፤ ስልሳ ስድስት ዘመን ሙሉ ቅጠሉ ሳይጠወልግ ደሙ ሳይደርቅ መኖር እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው?!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በዚያ የመከራ ዘመን ለእስራኤል ሁሉ የተዘጋጀውን መድኃኒት በእጇ ላይ ሲያስቀምጥላት ኢትዮጵያም ቅጠሉ እንዳይጠወልግ ደሙም እንዳይነጥፍ አድርጋ በሙዳይ ውስጥ ስታስቀምጥ ስንመለከት ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር የታመነች ሀገር እንደሆነች ያመላክታል፡፡ መድኃኒቱን ከእስራኤል እጅ አውጥቶ በኢትዮጵያ እጅ ማኖሩ ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር ሥራ የተመቸች ሀገር ስለሆነች ነው እንጅ ሌላ ምንድነው?
በሐዲስ ኪዳን የፈውስ ዛፍ መስቀል ነው፤ በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያዊው ሰው አቤሜሌክ በሙዳዩ ያስቀመጠው ከእስራኤላውያን እጅ የወጣው በኢትዮጵያውያን እጅ የገባው የፈውስ እንጨት ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ ዛሬ በታሪከ ኢትዮጵያ ታላቁን የመስቀልን በዓል እያከበርን ያለነው እንደ ሌሎቹ ሀገራት በክርስቶስ መስቀል አምሳል የተሠሩ መስቀላትን ይዘን አይደለም እራሱን የክርስቶስን መስቀል ይዛ ኢትዮጵያ መስቀሉን ታከብራለች፡፡ እንደ እመቤታችን ማርያም፣ እንደ ማርያም መግደላዊት ከመስቀሉ እግር ሥር ቆማ ኢትዮጵያ ስለመስቀሉ ‹‹ዮም መስቀል ተሰብሐ›› እያለች በያሬዳዊ ዜማ ትዘምራለች፡፡
ዓለም ቢያምንም ባያምንም ዛሬም ዓለም የሚድንበት የፈውስ እንጨት ያለው በኢትዮጵያ እጅ ነው፡፡ ወደ ቀድሞው ታሪክ ስንመለስ ሕዝቡ ወዲያውኑ መድኃኒቱን ሊቆርጥ የተላከው  ኢትዮጵያዊው ሰው ሳይመለስ በዚያች ክፉ ሌሊት ሕዝቡ ተማከው ፋርስ ባቢሎን ገብተው ስላደሩ ሳይጠቀሙበት ቀሩ፤ ዛሬም ዓለም በሰይጣን ተማርኮ ስለተወሰደ እግዚአብሔር ባዘጋጀለት መድኃኒት በቅዱስ መስቀል ባይጠቀምበትም ኢትዮጵያ ግን በልቧ ይዛው ትኖራለች፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች ስሙኝ!  በኋላም ቢሆን የማታ ማታ ለመላው ዓለም የመዳን ዐዋጅ የሚታወጀው ከዚህች ሀገር ነው ፡፡ ለእስራኤል ከሰባ ዓመት የስደት ቆይታ በኋላ የመመለሳቸው ዜና የተነገረው በኢትዮጵያዊው ሰው በአቤሜሌክ በኩል ነው፡፡ አሁንም ላለው ትውልድ እግዚአብሔር ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ የሚወጣበትን ዐዋጅ የሚያውጀው በኢትዮጵያ በኩል ነው፡፡ ሁልጊዜ ትኩስ የሆነው የጌታ ደም የሚፈስበት ፈውስ የማይነጥፍበት ቅዱስ መስቀል በእጇ ነውና፡፡
በእርግጥ ስለ መስቀል ስናሣ ኢትዮጵያ ከዚህም የሚቀድም ታሪክ አላት፡- ንግሥተ ሳባ ወደ ሰሎሞን በሄደች ጊዜ ከሰሎሞን ቤተ መንግሥት ወድቆ ያገኘቸው ግንድ እግሯ ላይ የወጣባትን ነውሯን እንዳስወገደላት እናውቃለን፡፡ ይህ ግንድ ባደረገው ተዓምራት የተነሣ እሷም እሱም አዋጥተው በብር ለብጠውታል፡፡ ከሰሎሞን በኋላ የተነሡ ነገሥታትም ይህን ግንድ በብር ይለብጡት ነበር፤ በቁጥር 28 የሚሆኑ ነገሥታት ከሰሎሞን በኋላ ነግሠዋል ከንግሥተ ሳባ እና ከሰሎሞን ጋር ሠላሳ ይሆናሉ፤ አይሁድ ጌታን የሚሰቅሉበት ጊዜ ሲደርስ ለይሁዳ የሰጡት ሠላሳ ብር የተገኘው ነገሥታቱ ለዚህ ግንድ ሲለብጡት ከኖሩት ነው፡፡
ብሩን ለይሁዳ ሰጥተው በግንዱ ጌታን ሰቀሉበት፤ ስለዚህ በመስቀሉ ከዓለም ቀድመን የተፈወስን እኛ መሆናችንን ተመልከቱ፤ ንግሥተ ሳባ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ትወክላለች እና፡፡ መስቀሉን በማክበርስ ከእኛ ከኢትዮጵያውያነ የሚቀድም ማነው? እኛ አይደለንም እንዴ ከሰሎሞን ቀድመን በብር ያስጌጥነው? መንፈስ ቅዱስ ኢትዮጵያን ጥንትም ቢሆን ሥራ እንደሚያሠራት ተመለክቱ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው እንጅ በእውነት ለግንድ ብር አውጥቶ የሚሸልም ማነው? ይህ በሰሎሞን ቤተ መመንግሥት በር ላይ የወደቀው ግንድ እንዲሁ እንደሌሎች ግንዶች አይደለም ይህን መንፈስ ቅዱስ ከገለጠላት ኢትዮጵያ በቀር ሌላ ማን ሊያውቅ ይችላል?
ዛሬስ ቢሆን መስቀሉን ኢትዮጵያ ስታከብረው መስቀሉን ከሌላው እንጨት መለየት አቅቷቸው እንደ ግብዝ የሚመለከቷት ሳይኖሩ ይቀራሉ ብላችሁ ነው? አባቶቻን ግን መንፈስ ቅዱስ ያለበማቸው ስለነበሩ ግብጻውያንን ዓባይን እንገድብባችኋለን ብለው በማንገራገር እጅ መንሻ እንስጣችሁ ሲሏቸው ከመስቀሉ በቀር ሌላ የሚያጠግባቸው እጅ መንሻ ቢያጡ መስቀሉን እጅ መንሻ አድርገው ተቀበሏቸው፤ ግብጽ አሳልፋ በረከቷን ለኢትዮጵያ ሰጠች፡፡ በእርግጥ ግብጽ ቀደም ሲል እንደነገርኋችሁ ስለመስቀሉ የኢትዮጵያን ያህከል ደጅ ጥናት አላደረገችም ኢትዮጵያ በንግሥተ ሳባ በኩል ለመስቀሉ እጅ መንሻ አቅርባለች፣ በአቤሜሌክ በኩል ስልሳ ስድስት ዘመን ሙሉ ስለ መስቀሉ ከሀገር ወጥታ ተሰዳለች፡፡ ስለዚህም አግዚአብሔር እውነተኛ ፍርድ ፈረደ፤ ደጅ የጠናችው ኢትዮጵያ በዐፄ ዳዊት ምክንያት መስቀሉን ተቀበለች፡፡
እሳቸውም መስቀሉ ስናር ላይ ሲደርስ መስቀሉን ሊቀበሉ ከመናገሻ ከተማቸው እንደወጡ ሳይመለሱ ቀሩ ሞት ወስዷቸዋልና፡፡ ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ መንበረ መንግሥታቸውን ሲረከቡ አባታቸው ዐፄ ዳዊት የጀመሩትንም ሥራ አብረው ተረከቡ፤ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አመጡ በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ከቤተ መንግሥታቸው ጎን ሊያኖሩት ተመኙ ልብ ላለው ሰው ከመስቀሉ አጠገብ መራቅ እንዴት ይከብዳል!? እመቤታችን፣ ጌታ የሚወደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ እናሌሎችም ቅዱሳን ያሉት በዚያ ነውና፡፡  እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ ወዳዘጋጀው ሥፍራ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ እንዲወስዱት በራዕይ አዘዛቸው፡፡ መስከረም አሥር ቀን ወደ ኢትዮጵያ የገባውን መስቀል መስከረም ሃያ አንድ ቀን በግሼን መስቀለኛ አምባ ላይ አስቀመጡት፡፡
ኢትዮጵያ መስቀላዊት ሀገር መስቀለኛ ተራራ የሚገኝባት ምድር፡፡    

Wednesday, 18 September 2019


የነፍሴ ጥያቄ
ያለ ጥያቄ በተፈጠረ ዓለም ውስጥ በጥያቄ የተሞላ ሕይወት ያለን የሆንነው ለምንድነው? ሳንጠይቅ ተፈጥረን ያለጥያቄ መሻታችን የማይፈጸምልን ለምንድነው? በውኑ ለምኖ ሰው የሆነ ከእኛ መካከል አለ? አጭር፣ ረጅም፣ ቀይ፣ ጥቁር ለመሆን ሀሳብ ያቀረበ ማነው? ማንም! አደል እንዴ!? ተሳሳትሁ?
ታዲያ ሳንለምን በተፈጠረ ሰውነታችን ውስጥ ጥያቄ ያለባት ነፍስ እንዴት ተገኘች? ነፍሳችን በራሷ ሳንለምነው እግዚአብሔር ከባሕርዩ ቸር መሆን የተነሣ ሕያዋን ይሁኑ ብሎ የሰጠን ስጦታ አይደለችምን? ዘፍ 2፥7 እስትንፋሱን ሳንለመነው የሰጠን አምላክ መልክዓ መለኮቱን ‹‹ሰውን በመልካችን በምሳሌአችን እንፍጠር›› ብሎ በገዛ ፈቃዱ መለኮቱን ይመስል ዘንድ ለፈቀደለት ሰው ‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል›› ሉቃ 11፥9፣ ዮሐ 14፥13፣ 15፥7 ብሎ ማስተማር ተገቢ ነው? ሳንለምነው ፈጥሮ እንዴት ለምኑ ይለናል?
እንዲያውም ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹ትመኛላችሁ አታገኙም በብርቱ ትፈልጋላችሁ ልታገኙ አትችሉም ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም›› ያዕ 4፥2 ማለቱ ያለ ልመና የምናሳካው ምንም ነገር የለም ማለቱ ነው? እግዚአብሔር የምሻውን የልቤን ጉዳይ ያውቀው የለ እንዴ? ለምንድነው እንደ ምድር ባለጠጎች እንድለምነው የሚያበረታታኝ ? ሳልለምነው ቢያደርግልኝ ምን ነበረበት? ጸሎትም ሲያስተምረኝ ልመና የተሞላበት ጸሎት አስተማረኝ፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ በደላችንን ይቅር በለን…ወደ ፈተና አታግባን ከክፉ ሁሉ አድነን ›› የሚል ልመና የሚበዛበት ጸሎት አለኝ ይሄ አግባብ ነውን?
በእርግጥ ጥያቄ ሁሉ ልመና አይደለም፤ እኔን ያስገረመኝ መቼ ነው ያለ ጥያቄ መኖር የሚቻለው? ከዚህ ደረጃ ላይ የደረሰስ ማነው? የምታውቁት ሰው አለ? ጥያቄዎቹ ሁሉ ተመልሰውለት በኅሊና ፀጥታ ውስጥ እየኖረ ያለ ሰው አለ? የሚለው ነው፡፡
የተወደዳችሁ የልዑል አምላክ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! እኔ በዚህ ርዕስ ውስጥ ማንሣት የፈለግሁት ያለ ጥያቄ ተፈጥረን ጉዟችንን እስከምናጠናቅቅ ድረስ በጥያቄ የተሞላ ኑሮ ይገጥመናል ጥያቄው አንዳንዱ የሚመለስ ሌላው ደግሞ የማይመለስ ሊሆን ይችላል ይህ ለምን ሆነ? ጠያቂ መሆናችንስ ጉዳት ይኖረው ይሆን? በነገራችን ላይ ይህ በሰው እና በመላእክት ሕይወት ውስጥ የሚታይ እንጅ ለሌላው ፍጥረት የለውምና ለእኛ ይህ መሰጠቱ ጉዳት ካለው እድንወያይበት ብየ ነው፡፡
ለጊዜው የነፍሴ ጥያቄ ያልኳቸው በኔ ውስጥ የሚመላለሱትን ነው በእናተም ውስጥ ያሉትን ንገሩኝ ቅዱሳን አበው፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች ጥያቄ የመለሰችውን መልስ እነግራችኋለሁ፡፡ 
 በዚህ ገጽ አስተያየት ለመስጠት ስለሚያስቸግር እኔም ለማየት ስለሚያስቸግረኝ simakone2006@gmail.com ብላችሁ መልዕክት ብታስቀምጡልኝ ደስ ይለኛል፡፡
    ?

Wednesday, 11 September 2019


ስለ አዲስ ዓመት ብሥራት ልነግራችሁ አሰብሁ ነገር ግን አዲሱን ዓመት በፊቴ ፈልጌ አጣሁት፤ አዲሱን ዓመት የሚያበሥሩን የኔቶቻችን አንዳንዶቹ ተገድለውብናል ያሉትም ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳይቃጠል በመጠበቅ ላይ ናቸው፤ ሰባቱን አዕዋዳት ዐውዶ፣ ቀመረ ድሜጥሮስን አቡሻኽርን አራቅቆ፣ በዓላቱን አጽዋማቱን አውጥቶ የሚነግረን ማነው? ሰማዩ ቦምብ እየወረወረብን ምድሩም አሸን እያፈላብን ከመከራ የሚያሳርፈን ምንም ሳይኖር ምን አዲስ ዓመት ልናውጅ እንችላለን፤ ማቅ በለበሰች አገር ውስጥ ሸማ ለብሰን የምናከብረው በዓል አይኖርም፡፡

 በዘጠናዎቹ መግቢያ አካባቢ የዲማ ጊዮርጊስ ተማሪ ነበርሁ፤ የዲማው ሊቅ የኔታ ዘሚካኤል ይሁኔ በዲማ ጊዮርጊስ በድምቀት የሚከበረውን የአቡነ ተክለ አልፋን በዓል ስናከብር የተቀደደ አሮጌ ልብስ ለብሰው ሲወጡ አንዱ ጓደኛችን ጠጋ ብሎ የኔታ! ‹‹ልብስዎ ተቀዷል በዚያ ላይ አዳፋ ልብስ ነው የለበሱት›› ሲላቸው ‹‹አይ ልጄ! ቤተ ክርስቲያን የመከራ ልብስ ለብሳ እኔ እንዴት ነጭ ልብስ እለብሳለሁ›› ሲሉት ትዝ ይለኛል፡፡ የኔታን ከዚያ ጉባኤ ተመርቄ እስከወጣሁበት ቀን ድረስ አንድም ቀን ነጭ ለብሰው አላየኋቸውም፡፡ 

ነጩ ልብስ ይበቃዋል አዲስ ዓመት ከመጣ ምን አልባት ያን ጊዜ ደሞ እንለብሰዋለን፡፡ ጣሊያንን ስንዋጋ ወደ ሰርግ እንደ ተጠራ ሰው ነጩን የሀገራችንን ሸማ ለብሰን ነበር አሁን ግን የምንዋጋው በዕለተ ዐርብ ሥርዓት ነውና ፀሐይ ጨረቃን መስለን ነው ማቴ 27፥45 አሁን ቤተ ክርስቲያን በምጥ ውስጥ ናት ከዚያም ከዚያም ላይ ሰይጣን ያጠመደው ወጥመድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያጠምድ የተጠመደ ነው፡፡ በእርግጥ ለቆቅ እና ለጅግራ ነው  እንጅ ለቁራ ወጥመድ አይጣልም፤ ለዓሣ ነው እንጅ ለእባብና ለዘንዶ መረብ አይዘረጋም፡፡ ሰይጣን በአሕዛብ ላይ ወጥመዱን የማይዘረጋው ስለዚህ ነው፡፡

 ቁራ ከመርከብ ወጥቶ ልክስክስ ነገር በሞላበት ምድር ወዲያ ወዲህ ሲል ወደ መርከቧ ሳይመለስ መቅረቱን ሰምተን ነበር ዘፍ 8፥7 ነገር ግን ቁራ በርግብ ላይ ጦርነት መክፈቱን አልሰማንም ነበር፤ ይሄ አዲስ ጦርነት ነው፤ ለኖኅ የምሥራችን ያበሠረች፣ የመርከቧን ነፍሳት ለሚበሉትም ለማይበሉትም የሰላም ዘመን ያወጀች ርግብ አልነበረችምን?

ዛሬ ከቁራ ጎን የቆሙ የማይበሉ እንስሳትም በሚበሉት እንስሳት ላይ የጨከኑ ይመስላሉ ቁራ በርግብ ላይ የከፈተው ጦርነት ያስደሰታቸው ይመስላል፤ ዓለምን መውረስ የሚቻለው ርግብ ባመጣችው የሰላም ወሬ ነው፡፡ ርግብ ባመጣችው የሰላም ዜና የተጠቀሙት የሚበሉትም የማይበሉትም እንስሳት እና አራዊት ናቸው

ርግቧ ቤተ ክርስቲያናችን ባስከበረችው አገር እና ድንበር የሚኖሩት ክርስቲያኖች ብቻ አልነበሩም ሁሉም በያዘው ዕምነት ጸንቶ ሲኖር ሀገሩን ግን አልተቀማም ነበር፤ ቤተ ክርስቲያ ቀብታ ባነገሠቻቸው መሪወቿ ጉልበት ተማምና ማንን አሳደደች? ሲኖዶስ ከፓርላማ በላይ የመወሰን ሥልጣን በነበረው ዘመን፣ አቡን እጨጌ ከጠቅላይ ሚንስትር በላይ ያዝዝ በነበረበት ዘመን ማንን በዋለበት አላሳድር ባደረበት አላውል ብለን ነበር? እስኪ ንገሩን አባቶቻችን በሠሩት ቅርስ ብቻችንን ከብረንበት እናውቃለን? የላሊበላን ሕንጻ ቤተ መቅደስ አደረግነው እንጅ የሀገር ሀብት አይደለም ብለን እናውቃለን? የአክሱምን ሐውልት በቤተ መቅደሱ ቅጥር ውስጥ በማኖራችን ጠበቅነው እንጅ ለብቻችን ከብረንበት እናውቃለን?

እኛ አገር ለማዳን ለሚመጣው ትውልድ በባርነት ውስጥ ያለች አገር አናወርስም ብለን ታቦት ይዘን አቡን ዕጨጌ ተከትለን ዐድዋ ላይ ስንዘምት እናንተ መቼም ጥቁር ሕዝብ ድል የለውም ጣሊያን ያሸንፋል ብላችሁ በማሰብ በከተማ የቀሩ የአርበኞችን ሚስቶች ልጆች እያረዳችሁ ሀብታቸውን እየዘረፋችሁ ስትቆዩ ከጦርነት መልስ ሊያጠፏችሁ የጀመሩ አርበኞችን መክራ ጠላትን እንደ ራስ መውደድ ይገባል በሚለው ሰማያዊ ቃሏ ለዘር ያተረፈቻሁ ይህች ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች አባቶቻችሁ አልነገሯችሁም?

    ሳላስበው ነገር ስቦኝ ጽሑፉን ከጀመርሁት በኋላ ሁኔታው አበሳጭቶኝ ብዙ ተናገርሁ እንጀ የዛሬ መልዕክቴ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች አዲስ ዓመት የመጣ መስሏችሁ አዲስ ልብስ ለብሳችሁ እንዳታከብሩ አደራ ለማለት ነው ዓላማዬ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የምሕረት ዘመን እስኪሆን ድረስ እንደ መርዶክዮስ ማቅ ለብስን በመሬት ላይ እንወድቃለን፡፡

ማስገንዘቢያ! ለዛሬው መልዕክቴ ርዕስ አልሰጠሁትም የሀገሬ ርዕስ ቤተ ክርስቲያን ነበረች ሀገሬ ኢትዮጵያ ርዕስ የሌላት የጉልበተኞች ድርሰት ሆና እኔ ለምን ርዕስ እሰጠዋለሁ ብየ ነው፡፡