ስለ አዲስ
ዓመት ብሥራት ልነግራችሁ አሰብሁ ነገር ግን አዲሱን ዓመት በፊቴ ፈልጌ አጣሁት፤ አዲሱን ዓመት የሚያበሥሩን የኔቶቻችን አንዳንዶቹ
ተገድለውብናል ያሉትም ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳይቃጠል በመጠበቅ ላይ ናቸው፤ ሰባቱን አዕዋዳት ዐውዶ፣ ቀመረ ድሜጥሮስን አቡሻኽርን
አራቅቆ፣ በዓላቱን አጽዋማቱን አውጥቶ የሚነግረን ማነው? ሰማዩ ቦምብ እየወረወረብን ምድሩም አሸን እያፈላብን ከመከራ የሚያሳርፈን
ምንም ሳይኖር ምን አዲስ ዓመት ልናውጅ እንችላለን፤ ማቅ በለበሰች አገር ውስጥ ሸማ ለብሰን የምናከብረው በዓል አይኖርም፡፡
በዘጠናዎቹ መግቢያ አካባቢ የዲማ ጊዮርጊስ ተማሪ ነበርሁ፤ የዲማው ሊቅ የኔታ
ዘሚካኤል ይሁኔ በዲማ ጊዮርጊስ በድምቀት የሚከበረውን የአቡነ ተክለ አልፋን በዓል ስናከብር የተቀደደ አሮጌ ልብስ ለብሰው ሲወጡ
አንዱ ጓደኛችን ጠጋ ብሎ የኔታ! ‹‹ልብስዎ ተቀዷል በዚያ ላይ አዳፋ ልብስ ነው የለበሱት›› ሲላቸው ‹‹አይ ልጄ! ቤተ ክርስቲያን
የመከራ ልብስ ለብሳ እኔ እንዴት ነጭ ልብስ እለብሳለሁ›› ሲሉት ትዝ ይለኛል፡፡ የኔታን ከዚያ ጉባኤ ተመርቄ እስከወጣሁበት ቀን
ድረስ አንድም ቀን ነጭ ለብሰው አላየኋቸውም፡፡
ነጩ ልብስ
ይበቃዋል አዲስ ዓመት ከመጣ ምን አልባት ያን ጊዜ ደሞ እንለብሰዋለን፡፡ ጣሊያንን ስንዋጋ ወደ ሰርግ እንደ ተጠራ ሰው ነጩን የሀገራችንን
ሸማ ለብሰን ነበር አሁን ግን የምንዋጋው በዕለተ ዐርብ ሥርዓት ነውና ፀሐይ ጨረቃን መስለን ነው ማቴ 27፥45 አሁን ቤተ ክርስቲያን
በምጥ ውስጥ ናት ከዚያም ከዚያም ላይ ሰይጣን ያጠመደው ወጥመድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያጠምድ የተጠመደ ነው፡፡ በእርግጥ ለቆቅ
እና ለጅግራ ነው እንጅ ለቁራ ወጥመድ አይጣልም፤ ለዓሣ ነው እንጅ
ለእባብና ለዘንዶ መረብ አይዘረጋም፡፡ ሰይጣን በአሕዛብ ላይ ወጥመዱን የማይዘረጋው ስለዚህ ነው፡፡
ቁራ ከመርከብ ወጥቶ ልክስክስ ነገር በሞላበት ምድር ወዲያ ወዲህ ሲል ወደ
መርከቧ ሳይመለስ መቅረቱን ሰምተን ነበር ዘፍ 8፥7 ነገር ግን ቁራ በርግብ ላይ ጦርነት መክፈቱን አልሰማንም ነበር፤ ይሄ አዲስ
ጦርነት ነው፤ ለኖኅ የምሥራችን ያበሠረች፣ የመርከቧን ነፍሳት ለሚበሉትም ለማይበሉትም የሰላም ዘመን ያወጀች ርግብ አልነበረችምን?
ዛሬ ከቁራ
ጎን የቆሙ የማይበሉ እንስሳትም በሚበሉት እንስሳት ላይ የጨከኑ ይመስላሉ ቁራ በርግብ ላይ የከፈተው ጦርነት ያስደሰታቸው ይመስላል፤
ዓለምን መውረስ የሚቻለው ርግብ ባመጣችው የሰላም ወሬ ነው፡፡ ርግብ ባመጣችው የሰላም ዜና የተጠቀሙት የሚበሉትም የማይበሉትም እንስሳት
እና አራዊት ናቸው
ርግቧ
ቤተ ክርስቲያናችን ባስከበረችው አገር እና ድንበር የሚኖሩት ክርስቲያኖች ብቻ አልነበሩም ሁሉም በያዘው ዕምነት ጸንቶ ሲኖር ሀገሩን
ግን አልተቀማም ነበር፤ ቤተ ክርስቲያ ቀብታ ባነገሠቻቸው መሪወቿ ጉልበት ተማምና ማንን አሳደደች? ሲኖዶስ ከፓርላማ በላይ የመወሰን
ሥልጣን በነበረው ዘመን፣ አቡን እጨጌ ከጠቅላይ ሚንስትር በላይ ያዝዝ በነበረበት ዘመን ማንን በዋለበት አላሳድር ባደረበት አላውል
ብለን ነበር? እስኪ ንገሩን አባቶቻችን በሠሩት ቅርስ ብቻችንን ከብረንበት እናውቃለን? የላሊበላን ሕንጻ ቤተ መቅደስ አደረግነው
እንጅ የሀገር ሀብት አይደለም ብለን እናውቃለን? የአክሱምን ሐውልት በቤተ መቅደሱ ቅጥር ውስጥ በማኖራችን ጠበቅነው እንጅ ለብቻችን
ከብረንበት እናውቃለን?
እኛ አገር
ለማዳን ለሚመጣው ትውልድ በባርነት ውስጥ ያለች አገር አናወርስም ብለን ታቦት ይዘን አቡን ዕጨጌ ተከትለን ዐድዋ ላይ ስንዘምት
እናንተ መቼም ጥቁር ሕዝብ ድል የለውም ጣሊያን ያሸንፋል ብላችሁ በማሰብ በከተማ የቀሩ የአርበኞችን ሚስቶች ልጆች እያረዳችሁ ሀብታቸውን
እየዘረፋችሁ ስትቆዩ ከጦርነት መልስ ሊያጠፏችሁ የጀመሩ አርበኞችን መክራ ጠላትን እንደ ራስ መውደድ ይገባል በሚለው ሰማያዊ ቃሏ
ለዘር ያተረፈቻሁ ይህች ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች አባቶቻችሁ አልነገሯችሁም?
ሳላስበው ነገር ስቦኝ ጽሑፉን ከጀመርሁት በኋላ ሁኔታው አበሳጭቶኝ ብዙ
ተናገርሁ እንጀ የዛሬ መልዕክቴ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች አዲስ ዓመት የመጣ መስሏችሁ አዲስ
ልብስ ለብሳችሁ እንዳታከብሩ አደራ ለማለት ነው ዓላማዬ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የምሕረት ዘመን እስኪሆን ድረስ እንደ መርዶክዮስ ማቅ
ለብስን በመሬት ላይ እንወድቃለን፡፡
ማስገንዘቢያ! ለዛሬው
መልዕክቴ ርዕስ አልሰጠሁትም የሀገሬ ርዕስ ቤተ ክርስቲያን ነበረች ሀገሬ ኢትዮጵያ ርዕስ የሌላት የጉልበተኞች ድርሰት ሆና እኔ
ለምን ርዕስ እሰጠዋለሁ ብየ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment