የነፍሴ ጥያቄ 4
?
በትዳር ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዴት ይቻላል?
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሴትና
ወንድ አድርጎ በመፍጠሩ ምን ታስባለህ? መልካም አደረገ ብለህ ታስባለህ? ወይስ እባብ በሴቲቱ በኩል አድርጎ ሞትን ወደ ዓለም በማምጣቱ
ሴትን መፍጠር አልነበረበትም ብለህ ታስባለህ? ስህተት ያጋጠመው ሰው አባታችን አዳም ‹‹ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርሷ
ሰጠችኝና በላሁ›› ዘፍ 3፥12 ብሎ እንደ ተናገረ መሳሳትህን በሴቲቱ ስታመካኝ ትኖራለህ? በትዳርህ ውስጥ ፈታኙ መግቢያ እንዳያገኝ እነዚህን አስብ ትዳርህ በሕይወት እንዲኖር እነዚህን ሰባት መልካም ሀሳቦች
በልብህ አዘውትራቸው፡፡
1.
ትዳር መልካም ነው በል
የመጀመሪያው ትልቁ ጥበብ እግዚአብሔር
የፈጠረውን ሁሉ መልካም እንደሆነ ማመን ነው፡፡ በታላቅ ብልሃት የሠራውን ሰው አራቱ ባሕርያት ቢጣሉበት የሚያስታርቅበትን ብልሃት
አስተማረው፤ ባሕርዩን በባሕርዩ እንዲያስታርቅ ከገንዛ ባሕርዩ ሴትን ፈጠረለት፡፡ እግዚአብሔር ቅድመ ዓለም ፍጥረት ሳይኖር ማን
ያመሰግነው ነበር? ብለህ ስትጠይቅ ሊቃውንቱ ባሕርዩን ባሕርዩ ያመሰግነው ነበር ይሉሃል አይደል? ሰውን ደግሞ አራቱ ባሕርያት ቢጣሉበት
ማን ያስታርቀዋል? ያልኸኝ እንደሆነ ባሕርዩን ባሕርዩ ያስታርቅለታል እልሃለሁ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡- በሰው ባሕርይ
ውስጥ ቁጣ፣ ትዕግሥት፣ ረሀብ፣ ጥም፣ እንቅልፍ፣ ድካም፣ ዝሙት የመሳሰሉት ሁሉ ዝም ብለው የሚደረጉ እንዳይመስሉህ አራቱ ባሕርያት
እርስ በእርስ አልስማማ ሲሉ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ታዲያ ለእነዚህ ባሕርያቶቻችን ማስታረቂያ ከባሕርያችን የተከፈለች ሴትን ለአዳም
ሰጠው፡፡ ሴት ማለት አንተ ነህ፤ እግዚአብሔር ለአዳም ሴትን ሲሰጠው ራሱን ለራሱ ሰጠው፤ አዳምም ነቅቶ ‹‹አጥንቷ ከአጥንቴ ሥጋዋም
ከሥጋዬ ነው›› ማለቱ ከእርሱ የተገኘች እንደሆነች ተገልፆለት ነው፡፡ ከባዕድ ፍጥረት ጋር ወይም ከሌላ ሁለተኛ አካል ጋር እየኖርህ
እንደሆነ አታስብ፤ ከአንተ አካል ከፍሎ ከአንተ ጋር አንድ ሥጋ ካደረጋት ሴት ጋር እየኖርህ ነው ‹‹ በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም
አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› ዘፍ 2፥24 እንዲል
በትዳር ውስጥ የሚኖር ሰው እግዚአብሔር
ባዘጋጀለት መንገድ የሚጓዝ መንገደኛን ይመስላል፤ አራቱን ባሕርያቱን
በተሰጠችው ሚስቱ እያለዘበ፤ ለነፍስ እያስገዛ እስከ እግዚአብሔር መንግሥት ድረስ ይደርሳል፡፡ ትዳርህን ውደደው ምን አልባትም አሁን
የማትወደውን ሕይወት እየኖርህ ያለህም እንኳን ቢሆን ወደ ምትወደው እግዚአብሔር ለመድረስ ከዚህ የተለየ ለአንተ የተዘጋጀ መንገድ
እንደሌለ እወቅ፤
መልካም በሆነው በዚህ መንገድ ስትጓዝ
በአንተም ሆነ በሚስትህ ላይ ክፉ ሀሳብ መንገዳችሁን የዘጋባችሁ መልካም የሆነውን እግዚአብሔርን ተዋሕዳችሁት እንዳትኖሩ ሰይጣን
ስለሚፈልግ ነው፡፡
በብህትውና በምንኩስና ብትኖር እግዚአብሔርን
ትመስለዋለህ፤ በትዳርም ብትኖር ሕገ እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ ሕጉን እየፈጸምህ እግዚአብሔርን ተዋሕደኸው ትኖራለህ፡፡
እግዚአብሔር መልከ ጼዴቅን ባሕታዊ አድርጎ ዓለምን ባረከበት፤ አብርሃምን ባለትዳር
አድርጎ ዓለምን አዳነበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብርሃም በተወለደው ልደት በመልከ ጼዴቅ ክህነት ዓለምን አድኖታልና፡፡ እንደ
መልከጼዴቅ መሆንን ብቻ እግዚአብሔር ቢያዝዝ ኖሮ የእግዚአብሔር መልካምነት ከወዴት አለ? ነገር ግን መልካሙ አባት ለሰው የምትሻለውን
መልካም ነገርን አደረገ እሷም ሚስት ናት - ሚስትን ሰጠው፡፡
መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ያገባ መልካ ነገርን አደረገ›› 1ቆሮ 7፥38
ማለቱን አስተውል አንተ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መልካም ነገርን በማድረግ ላይ እንደሆንህ እየመሰከረልህ ነው ማለት ነው፡፡
ትናትና ባንተና በሚስትህ መካከል የማይገባ ነገር እንዲፈጠር ያደረገው አንተም እሷም ሳትሆኑ ሰይጣን ነው፡፡ እሷ መልካም ነበረች
ለዚህ ምስክሩ ደግሞ አንተው ነህ ስታገባትኮ መልካምነቷን አይተህ ከዓለም ሴቶች ሁሉ መርጠህ እንደገባሃት የታወቀ ነው ስለዚህ ለመልካምነቷ
ምስክሩ አንተው ነህ፡፡ ይልቁንስ ሚስትህ መልካም እንዳልሆነች አታስብ ትዳር መልካም እንዳልሆነ አድርገህም ለሰዎች አትናገር ትዳር
መልካም ነውና፡፡
ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የምትረዳት
አንዲት የታመመች መነኩሲት ነበረች ይላል ገድሏ፤ ራሷን መርዳት የማትችል ስለነበረች በሥርዓተ ገዳም መሠረት የሚረዳት አንድ ሰው
ይመደብላታል፤ ነገር ግን ይህች ሴት ሊረዷት የተመደቡላትን ሁሉ በክፉ ግብሯ ታሳድዳቸው ስለነበረ ማንም ረጅም ጊዜ ሊረዳት አልቻለም፤በመጨረሻ
ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ልትረዳት ጀመረች እንደተለመደው በክፉ ግብሯ ፀናች ምግብ ስታመጣላት አንች በልተሸ በልተሸ ሲተርፍሽ አመጣሽልኝ
ትላታለች በወጣች በገባች ቁጥር በዓለም ላይ ያሉ ስድቦችን ሁሉ ትሰድባታለች ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ግን ትታገሣት ነበር እንጅ አንድም
ቀን ክፉ ቃል አትናገራትም ነበር፤ እህቶቿ መነኮሳይያቱ ይህን አይተው ለምን አትተያትም ለምን ትታገሻታለሽ? አሏት፡፡ እሷም ምን
አደረገችኝ? ምን አጠፋች? አለቻቸው፤ ባንች ላይ የምትናገረውን ክፉ ቃል ሁሉ አትሰሚምን? አሏት እሷም መልሳ እኔስ ክፉ ግብሯን
ባየሁ ጊዜ ከሰይጣን እንጅ ከእሷ እንዳልሆነ ስለማስብ በጠላቴ በሰይጣን እንጅ በእሷ ተቀይሜ አላውቅም ከረዳችሁኝ ጠላቴ ሰይጣንን
እንዳባርረው እርዱኝ ብላ ለእህቶቿ መነኮሳት መለሰችላቸው፡፡
አንተም እንዲህ በል! ትናንት ክፉ
ነገር የተናገረችኝ ክፉውን ሁሉ ያደረገችብኝ እሷ ሳትሆን ጠላቴ ሰይጣን ነው በልና ሰይጣንን ተቀየመው እንጅ ሚስትህን አትቀየማት፤
ከቻልህ ሚስትህን ሳይሆን ባንተ ላይ መልካም ሕይወት እንዳይኖር ያደረገ ሰይጣንን አስወጥተህ ስደደው እንጅ ሚስትህን ለምን ትሰዳታለህ?
ሚስትህን መፍታትን ካሰብህ መልካም ነገርን ለይተህ አታውቅም ማለት ነው፤ ‹‹ያገባ መልካም ነገርን አደረገ›› ብሎ መምህርህ ቅዱስ
ጳውሎስ መስክሮልህ እንዴት ‹‹እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር መፋታትን እጠላለሁ›› ሚል 2፥16 ወደ ተባለው የተጠላ ተግባር ትመለሳለህ?
አስተውል! ባንተና በእሷ መካከል ያለው ክፉ ነገር ሁሉ አንተም እሷም ሳታውቁ ጠላት ሰይጣን የሠራው ነው እንጅ አንተም እሷም ይህን
አላደረጋችሁትም፡፡
ሁለት መነኮሳት በበረሃ ይኖሩ ነበረ
ብዙ ዘመናት ብቻቸውን በበረሃ ውስጥ በጥሩ ፍቅር ከቆዩ በኋላ መጣላት ጀመሩ የመጣላታቸው ምክንያቱ ደግሞ ያንደኛው መነኩሴ በትር
መጥፋቷ ነው፤ ብቻቸውን እየኖሩ የሰው ፊት አይተው አያውቁም ማን ወሰደው ብለው ሲፈልጉ አጡት በትሩ የጠፋችበት መነኩሴ ለብዙ ዘመናት
አብሮት የኖረ ወንድሙን ተቀየመው ካንተና ከእኔ በቀር በዚህ በረሃ ማን ይኖራል? ሰብረህ ጥለህብኝ ነው እንጅ ሌላ ማን ይወስደዋል?
አለው እያደር ፍቅራቸው እየጠፋ መለያየታቸው እየሰፋ ሄደ በመጨረሻ በትሩ የጠፋበት መነኩሴ ተነሥቶ በቃ ካንተ ጋር መኖር ፈተና
ሁኖብኛልና ተወኝ በዓቴን ለቅቄ ልወጣ ነው አንተ ኑርበት አለው ወንድሙም ከእግሩ ላይ ወድቆ ይቅርታ አድርግልኝ እኔ ይህን አላደረግሁትም
በዓትህን ለቀህ አትሂድ እንዳስለመድነው አብረን በፍቅር እንኑር ብሎ ለመነው እሱ ግን እምቢ አለና ወጥቶ ሊሄድ ሲዘጋጅ እንዴት
ወንድሜ በሰይጣን ፈተና በዓቱን ለቆ ሲሄድ ዝም እላለሁ ብሎ ተንበርክኮ ጸሎት አደረገ ያንጊዜ መልአኩ መጥቶ ይህን ያደረገው እርሱ
አይደለም፤ ሰይጣን ይህን አደረገው ብሎ ያንን ሰይጣንን በእሳት ጅራፍ እየገረፈ የደበቀውን በትር እንዲያመጣ አዘዘው ሰይጣንም እየቀባጠረ
በትሩን ወርውሮላቸው ሄደ እነሱም እንደ ቀደመው ሁነው በፍቅር መኖር ጀመሩ፡፡
ከዚህ ተማሩ ክፉ ነገርን ሁሉ እናንተ
አላደረጋችሁትም ትናንት እጃችሁ ላይ የነበረው ምርኩዛችሁ የጠፋው በእናንተ አይደለም ሰይጣን ሲከታተላችሁ ኑሮ ይህን አደረገባችሁ፤
ስለጠፋው በትር ስትከራከሩ እጃችሁ ላይ ያለችውን መንግሥተ ሰማያትን ለምን ታጣላችሁ?
ወንድሜ ትዳር መልካም ነው በል!
2. ትዳር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው
ይቀጥላል…..
No comments:
Post a Comment