የእግዚአብሔር ማደሪያ
‹‹ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ ነፍሴ አትፀየፋችሁም በመካከላችሁም እሄዳለሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ
እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛችሁ›› ዘሌ 26፥11 ‹‹የምስክሩ ድንኳን፣ የመገናኛ ድንኳን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ›› የሚለው ሦስቱም
ስያሜ የተሰጠው ሙሴ ያዘጋጀው ድንኳን ነው፡፡ ዘፀ 29፥42፣ ዘኁ 17፥7፡፡
ይህ ድንኳን ጠቅላላ ስፋቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን ሃያው ክንድ ቅድስት፣ አሥሩ ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን ይባላል፡፡ በሃያው
ክንድ ካህናት ዘወትር አገልግሎታቸውን ይፈጽሙበታል፤ በአሥሩ ክንድ ግን ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ጊዜ ዕለተ ዮሴፍ የሚባል አላቸው
በጥቅምት ጨረቃ በአሥረኛው ሠርቅ የሚከበር ነው በዚያ ቀን መሥዋዕት የሚሠዋው ሊቀ ካህናት ብቻ ይገባባታል እንጅ ማንም ወደ ቅድስተ
ቅዱሳን መግባት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ‹‹ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በኋለኛይቱ
ድንኳን ግን ሊቀ ካህናት ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል›› ዕብ 9፥6-7 እንዲል፡፡
በቅድስቱ ውስጥ መቅረዙ፣ መሠዊያው፣ መሥዋዕቱ ይገኝባታል በቅድስተ ቅዱሳኑ ደግሞ ማዕጠንተ ወርቅ፣ ጽላቱ፣ መሶበ ወርቅ፣
በትረ አሮን ይገኛሉ፡፡
-
መቅረዙ በሠርክ ይበራል በማለዳ ይጠፋል ስድስት የፈትል ማስቀመጫ (ምንባረ
ፈትል) በሁለቱ ጎን ነበረው፤ በስድስቱ የፈትል ማስቀመጫዎች መካከል ያለ ሥረ ወጥ የፈትል ማስቀመጫ አለ ካህኑ ዘይቱን የሚጨምረው
በመካከል ባለው በሥረ ወጡ ነው፤ ከላይ እስከታች ያሉት አዕፁቅ (የፈትል ማስቀመጫዎች) ዘይት የሚያገኙት ከዚህ ከመካከለኛው (ከሰባተኛው
የፈትል ማስቀመጫ) ነው ማለት ነው፡፡ በአፍኒንና በፊንሐስ ዘመነ ክህነት ካልሆነ በቀር በዚህ መቅረዝ ላይ መብራት በሌሊት ተለይቶት
አያውቅም፡፡
-
መሠዊያውና መሥዋዕቱም (ሰደቃ) የሠርክና የነግህ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ነው፡፡ በቅድስቱ ውስጥ መሆኑም ስለዚህ ነው በየቀኑ
መሥዋዕት የሚቀርብበት ስለሆነ፡፡ ባዶ አይሆንም የነግሁን በልተው የማታ መሥዋዕት ሠውተውበት ይሄዳሉ፡፡ አሥራ ሁለት ሕብስተ ገጽ
ነው በቀን የሚያቀርቡት፡፡ ስድስቱን ማለዳ ያቀርቡታል ስድስቱን ለማታ መሥዋዕት አዘጋጅተው ይሄዳሉ እንጅ ሰደቃው ባዶ አይሆንም
ነበር፡፡
-
ማዕጠንተ ወርቁ እና የዕጣን መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይገኛሉ ሊቀ ካህናቱ በዓመት ሲገባ የዕጣን መሥዋዕት የሚያቀርብባቸው
ናቸው፤ ካህኑ ዘካርያስ ቅዱስ ገብርኤልን ያየው በዚህ መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ነው ሉቃ 1፥11
-
ሁለንተናዋ በወርቅ የተለበጠችው ታቦት በእርሷም ላይ ሙሴ የሳላቸው ኪሩቤል እንዲሁም መለወጥ የሌለበት የእስራኤል መና ያለባት
መሶበ ወርቅ እና የአሮን የካህንነቱ ምስክር የሆነችው የአሮን በትር በዚህ ቅዱስ ክፍል ይገኛሉ፡፡
·
የወርቁ መሠዊያ መሥዋዕቱ ይቀርብበታል፣
·
በታቦቱ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝበታል፤
·
በትረ አሮንና በመሶበ ወርቁ ምልክቶች ናቸው፡፡ ሳይተክሏት የምታፈራዋ ውኃ
ሳያጠጧት የምታፈራዋ የአሮን በትር ያለ ዘርዓብእሲ በድንግልና ፀንሳ የምትወልደውን እመቤታችንን ትሰብካለች መሶበ ወርቁም ዘመን
ሳይሰፈርለት የሚኖረውን አማናዊውን መሥዋዕታችንን ክርስቶስን ያመለክታል፡፡
የመገናኛው ድንኳን በስተምሥራቅ በኩል የሚገኝ አንድ በር ነበራት፤ እንግዲህ ስንቱን እነግራችኋለሁ ምሰሶወቿን፣ መጋረጃዋን፣
ቁልፎቿን፣ ከሐር መጋረጃ እንዲሠራ የታዘዘውን አጥሯን፣ ካስማዎቿን አውታሯን ስንቱን አነሣዋለሁ፡፡ እንዲሁ መንገደኛ ነኝና የቀናኝን
እያነሣሣሁ አልፋለሁ፡፡ እናንተ ግን በቦታው ተገኝታችሁ ብትጎበኙት መልካም ነው ከዘፀ 25 እስከ ዘፀ 40 ድረስ በሰፊው ተመዝግቧል፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከተበተኑበት መሰብሰብ፣ ከባርነት ቤት ወደ ነጻነት፣ ከስደት ወደ ርስት በመለሰበት ወቅት ሕዝቡ
እርሱን የሚያገኙበት፤ እርሱም ሕዝቡን የሚያገኝበት መገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው ‹‹በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስ ሥሩልኝ››
ዘፀ 25፥8 ከከብሩ የተነሣ ሰማይ ማደሪያው ይሆን ዘንድ አይችልም ነገር ግን በሰው ፍቅር ምክንያት የሚያድርበት ድንኳን እንዲያዘጋጁለት
እስራኤልን አዘዛቸው፤ ይህ ፍቅር ታላቅ ነው፤ በሰማይ ዙፋኑን የዘረጋ እግዚአብሔር በስደተኛ ሕዝብ መካከል ሊያድር መቅደስ አስገነባ
ያን ጊዜ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ ሁለት ዓመት ሆኗቸው ነበረ፤ በምድረ በዳ ላለ ሕዝብ ከዚህ የሚበልጥ ምን ደስታ አለ? ለአራት
መቶ ዓመት በገነቡት ከተማ ውስጥ እግዚአብሔር መቅደስ እንዲገነቡለት አላዘዛቸውም ነበር ከተማው ለእርሱ ማደሪያ የሚሆን አልነበረምና
ምድረ በዳውን መረጠ፡፡
የሕዝቡስ ነገር አይገርማችሁም? ይሄ ስደተኛ ሕዝብ ያለውን ሁሉ አምጣ ተብሎ ሲጠየቅ ምንም አልከለከለም ሁሉን ሰጠ ወርቅ፣
ብር፣ ነሐስ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ ግምጃ፣ የበፍታ መጋረጃ ሌሎችም ማንም በልቡ ያሰበውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ይሠራበት ዘንድ
አመጣ እንጅ በመንገድ ሳለሁ ምን አለኝ? አላለም፡፡ ለሚሠራው ሰው ለሙሴም ድንኳኑን በሰማያዊው ድንኳን አምሳል እንዲያዘጋጀው ወደ
ደብረ ሲና ወስዶ ለአርባ ቀናት ሰማያዊውን ድንኳን አስጎበኘው ከብርሃን የተሠራውን፣ የእሳት መጋረጃ ያለውን፣ የውኃ መርገፍ፣ የእሳት
ክዳን ያለውን፣ በመብረቅ የታጠረውን ሰማያዊ ማደሪያውን አሳየው፡፡ በዚያው አምሳል በምድር ያለውን ማደሪያውን ይሠራለት ዘንድ አዘዘው፤
ቅዱስ ያሬድ ይህን ድንኳን የሰማይ ሁለተኛ ያደርገዋል ‹‹ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ
ለቅድስት ደብተራ፤ የጽዮን በኵር አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ሁለተኛም ልዩ የሆነች ድንኳኑን እንዴት እንዴት እንደሚሠራት ለሙሴ አሳየው››
ብሎ በዜማ ይቀኛል፡፡
አሠራሯ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ ሥራዋ ግን በምድራውያን ሰዎች እጅ የተፈጸመ ይህች የመገናኛ ድንኳን እመቤታችን
ናት፤ በሰዎች መካከል ያለች ቤተ መቅደሱ ሰባት የእሳት መጋረጃ ያላት፣ ፊቷ ወደ ምሥራቅ የዞረ፣ አንድ ክርስቶስ ብቻ የሚገባባት
አንድ በር ያላት፣ ያውም ሕዝቅኤል እንዳየው ለዘለዓለም ታትሞ የሚኖር በር ሕዝ 44፥1 ማዕጠንተ ወርቁ፣ መሶበ ወርቁ፣ መቅረዙ፣
ማዕዱ ሰባቱ ንዋያት የሚገኙባት በሠርክም በነግህም መሥዋዕት የማይታጎልባት አማናዊት ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ናት፡፡
ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጀርባዋን ለምዕራብ አድርጎ መሥራቱ እመቤታችን ከምሥራቅ ይመጣል ዕን 3፥3 ተብሎ የተነገረውን
መሢህ የምትጠብቅ ሲኦል ገሐነም የማይቀበላት ለአንድ ሊቀ ካህናት መግቢያ የተዘጋጀች ባለ አንድ በር ቤተ መቅደስ መሆኗን ያመለክታል፡፡
እስራኤል ሁሉ እግዚአብሔርን በክብር ተገልጦ የሚያዩት ከደብረ ሲና በኋላ በዚህ መገናኛ ድንኳን ነበረ፤ ጠላት የበረታበት የሚያመልጥባት፣
ብርቱ ጠላት የሚሸነፍባት ይህች ድንኳን ምዕመናን አጋንንትን ድል የነሡባት አጋንንትም ድል የተነሡባትን አማናዊቷን የእግዚአብሔር
ማደሪያ ድንኳን እመቤታችንን ያመለክተናል፡፡ ዘኁ 16፥42
እግዚአብሔር ስደተኛውን ሕዝብ የገነባውን ከተማ የሠራውን ቤት አስጥሎታልና የመጀመሪያውን ቤቱንም አፍርሶበታልና ሌላ
አዲስ ቤት በሰማያዊው ቤተ እግዚአብሔር አምሳል ሠራላቸው፤ ይገርማል! ከፈርዖን ጋር ከመኖር ከእግዚአብሔር ወደ መኖር፣ ከግብጻውያን
ጋር ከማደር ከኪሩቤል ጋር ወደ መነጋገር፣ ‹‹ሂዱ ጡብ እርገጡ፣ ሥሩ ከጡቡ ቁጥር ምንም አያጎሉላችሁም፣ጭድም አይሰጧችሁም›› ዘፀ
5፥18 ከሚለው ክፉ ድምጽ ለይቶ ከሥርየት መክደኛው የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ወደ መስማት መለሳቸው፡፡
በእርግጥ ሕዝቡ ይህ ሁሉ ቢሆንላቸውም ወደ ጣዖት ወደ ኃጢአት ማዘንበላቸው አልቀረም ለእግዚአብሔር መባውን ልባቸው እንደ
ፈቀደ ያመጡትን ያክል ለጣዖቱም ሥራ በእጃቸው በጣታቸው እና በጆሯቸውም ያለውን ጌጣቸውን ማምጣታቸው አልቀረም፤ ዘፀ 32፥2 በእግዚአብሔር
ማደሪያ ዙሪያ ሰፍረው እየኖሩ ሞት እየነጠቀ ጨረሳቸው ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ መንገዱን የሞት መንገድ አደረጉት፤ የተስፋይቱን ምድር
የሚወርሰውን ትውልድ በመንገድ አዘገዩት፡፡
በመጨረሻም፡- ይህ ድንኳን በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ገባ፤ እግዚአብሔር
ኢትዮጵያ ውስጥ ድንኳን ሥሩልኝ አላለም መላዋ ኢትዮጵያ ድንኳኑ ናትና፡፡ እስራኤልን በደጅ ጽናቷ ያሸነፈችው ሙሽራዋ ኢትዮጵያ በመጨረሻ
የእስራኤልን ክብር ከእስራኤል ቀምታ ወሰደች፤ እስራኤል የማይገባት ስለሆነ ብኵርናዋን ለኢትዮጵያ ለቀቀች፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን
ማደሪያው መሆኗን ይታወቅ ዘንድ በመናገሻዋ ከተማ አክሱም ገብቶ የነገሠበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ ንጉሥ ማደሪያ፡፡ የአክሱም
የሕንደኬ ንግሥታት፣ እነ አቤሜሌክም ለደጅ ጥናታችን ማረጋገጫ ናቸው፡፡
1ነገ 10፥1፣ ሥራ 8፥27፣ ተረፈ ኤር. 8፥8 ለዚህ ነው ዛሬ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
Ø ታቦት
Ø በእስራኤል ምድር የሚገኙ በኵሮች ሁሉ
Ø ሌዋውያኑ ዛሬ ወደ ሀገራችን መናገሻ ከተማ አክሱም የገቡበት ቀን ነው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሕገ ኦሪት ተሸጋገርን ወደ ክርስቶስ መርታ የምታደርሰንን ቅድስት ኦሪትን የተቀበልን
ዛሬ ነው፤ በወርቅ የተለበጠውን ጽላት ከነ ሌዋውያኑ ኦሪቱን ከነ መተርጉማኑ ተሰጠን፡፡ የብሉይ ኪዳን ድኅነት ለሁሉ መሆን አይችልምና
እኛ ቅዱሳት ንዋያቱን ስንቀበል እስራኤል ባዶ ሆነች፡፡ ግብጻውያን በኃይለ እግዚአብሔር ተረትተው በኵሮቻቸውን አጡ፤ እስራኤል በሃይማኖት
ድል ተነሥታ በኵሮቿን ለኢትዮጵያ ሰጠች፡፡ ከዛሬ ጀምሮ የሰሎሞን በኩር ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ ይነግሣል፡፡ እግዚአብሔር
የማለላት የዳዊት ዙፋን በኋላም የእግዚአብሔር ልጅ የወረሳት የዳዊት ምንግሥት በኢትዮጵያ ተዘረጋች፡፡ መዝ 131፥11
No comments:
Post a Comment