>

Saturday, 7 December 2019


የነፍሴ ጥያቄ 4
?
በትዳር ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዴት ይቻላል?
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሴትና ወንድ አድርጎ በመፍጠሩ ምን ታስባለህ? መልካም አደረገ ብለህ ታስባለህ? ወይስ እባብ በሴቲቱ በኩል አድርጎ ሞትን ወደ ዓለም በማምጣቱ ሴትን መፍጠር አልነበረበትም ብለህ ታስባለህ? ስህተት ያጋጠመው ሰው አባታችን አዳም ‹‹ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ሰጠችኝና በላሁ›› ዘፍ 3፥12 ብሎ እንደ ተናገረ መሳሳትህን በሴቲቱ ስታመካኝ ትኖራለህ? በትዳርህ ውስጥ ፈታኙ መግቢያ እንዳያገኝ እነዚህን አስብ ትዳርህ በሕይወት እንዲኖር እነዚህን ሰባት መልካም ሀሳቦች በልብህ አዘውትራቸው፡፡
1.   ትዳር መልካም ነው በል
የመጀመሪያው ትልቁ ጥበብ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሁሉ መልካም እንደሆነ ማመን ነው፡፡ በታላቅ ብልሃት የሠራውን ሰው አራቱ ባሕርያት ቢጣሉበት የሚያስታርቅበትን ብልሃት አስተማረው፤ ባሕርዩን በባሕርዩ እንዲያስታርቅ ከገንዛ ባሕርዩ ሴትን ፈጠረለት፡፡ እግዚአብሔር ቅድመ ዓለም ፍጥረት ሳይኖር ማን ያመሰግነው ነበር? ብለህ ስትጠይቅ ሊቃውንቱ ባሕርዩን ባሕርዩ ያመሰግነው ነበር ይሉሃል አይደል? ሰውን ደግሞ አራቱ ባሕርያት ቢጣሉበት ማን ያስታርቀዋል? ያልኸኝ እንደሆነ ባሕርዩን ባሕርዩ ያስታርቅለታል እልሃለሁ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡- በሰው ባሕርይ ውስጥ ቁጣ፣ ትዕግሥት፣ ረሀብ፣ ጥም፣ እንቅልፍ፣ ድካም፣ ዝሙት የመሳሰሉት ሁሉ ዝም ብለው የሚደረጉ እንዳይመስሉህ አራቱ ባሕርያት እርስ በእርስ አልስማማ ሲሉ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ታዲያ ለእነዚህ ባሕርያቶቻችን ማስታረቂያ ከባሕርያችን የተከፈለች ሴትን ለአዳም ሰጠው፡፡ ሴት ማለት አንተ ነህ፤ እግዚአብሔር ለአዳም ሴትን ሲሰጠው ራሱን ለራሱ ሰጠው፤ አዳምም ነቅቶ ‹‹አጥንቷ ከአጥንቴ ሥጋዋም ከሥጋዬ ነው›› ማለቱ ከእርሱ የተገኘች እንደሆነች ተገልፆለት ነው፡፡ ከባዕድ ፍጥረት ጋር ወይም ከሌላ ሁለተኛ አካል ጋር እየኖርህ እንደሆነ አታስብ፤ ከአንተ አካል ከፍሎ ከአንተ ጋር አንድ ሥጋ ካደረጋት ሴት ጋር እየኖርህ ነው ‹‹ በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› ዘፍ 2፥24 እንዲል
በትዳር ውስጥ የሚኖር ሰው እግዚአብሔር ባዘጋጀለት መንገድ የሚጓዝ መንገደኛን ይመስላል፤ አራቱን  ባሕርያቱን በተሰጠችው ሚስቱ እያለዘበ፤ ለነፍስ እያስገዛ እስከ እግዚአብሔር መንግሥት ድረስ ይደርሳል፡፡ ትዳርህን ውደደው ምን አልባትም አሁን የማትወደውን ሕይወት እየኖርህ ያለህም እንኳን ቢሆን ወደ ምትወደው እግዚአብሔር ለመድረስ ከዚህ የተለየ ለአንተ የተዘጋጀ መንገድ እንደሌለ እወቅ፤
መልካም በሆነው በዚህ መንገድ ስትጓዝ በአንተም ሆነ በሚስትህ ላይ ክፉ ሀሳብ መንገዳችሁን የዘጋባችሁ መልካም የሆነውን እግዚአብሔርን ተዋሕዳችሁት እንዳትኖሩ ሰይጣን ስለሚፈልግ ነው፡፡
በብህትውና በምንኩስና ብትኖር እግዚአብሔርን ትመስለዋለህ፤ በትዳርም ብትኖር ሕገ እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ ሕጉን እየፈጸምህ እግዚአብሔርን ተዋሕደኸው ትኖራለህ፡፡
 እግዚአብሔር መልከ ጼዴቅን ባሕታዊ አድርጎ ዓለምን ባረከበት፤ አብርሃምን ባለትዳር አድርጎ ዓለምን አዳነበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብርሃም በተወለደው ልደት በመልከ ጼዴቅ ክህነት ዓለምን አድኖታልና፡፡ እንደ መልከጼዴቅ መሆንን ብቻ እግዚአብሔር ቢያዝዝ ኖሮ የእግዚአብሔር መልካምነት ከወዴት አለ? ነገር ግን መልካሙ አባት ለሰው የምትሻለውን መልካም ነገርን አደረገ እሷም ሚስት ናት - ሚስትን ሰጠው፡፡
    መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ያገባ መልካ ነገርን አደረገ›› 1ቆሮ 7፥38 ማለቱን አስተውል አንተ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መልካም ነገርን በማድረግ ላይ እንደሆንህ እየመሰከረልህ ነው ማለት ነው፡፡ ትናትና ባንተና በሚስትህ መካከል የማይገባ ነገር እንዲፈጠር ያደረገው አንተም እሷም ሳትሆኑ ሰይጣን ነው፡፡ እሷ መልካም ነበረች ለዚህ ምስክሩ ደግሞ አንተው ነህ ስታገባትኮ መልካምነቷን አይተህ ከዓለም ሴቶች ሁሉ መርጠህ እንደገባሃት የታወቀ ነው ስለዚህ ለመልካምነቷ ምስክሩ አንተው ነህ፡፡ ይልቁንስ ሚስትህ መልካም እንዳልሆነች አታስብ ትዳር መልካም እንዳልሆነ አድርገህም ለሰዎች አትናገር ትዳር መልካም ነውና፡፡
ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የምትረዳት አንዲት የታመመች መነኩሲት ነበረች ይላል ገድሏ፤ ራሷን መርዳት የማትችል ስለነበረች በሥርዓተ ገዳም መሠረት የሚረዳት አንድ ሰው ይመደብላታል፤ ነገር ግን ይህች ሴት ሊረዷት የተመደቡላትን ሁሉ በክፉ ግብሯ ታሳድዳቸው ስለነበረ ማንም ረጅም ጊዜ ሊረዳት አልቻለም፤በመጨረሻ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ልትረዳት ጀመረች እንደተለመደው በክፉ ግብሯ ፀናች ምግብ ስታመጣላት አንች በልተሸ በልተሸ ሲተርፍሽ አመጣሽልኝ ትላታለች በወጣች በገባች ቁጥር በዓለም ላይ ያሉ ስድቦችን ሁሉ ትሰድባታለች ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ግን ትታገሣት ነበር እንጅ አንድም ቀን ክፉ ቃል አትናገራትም ነበር፤ እህቶቿ መነኮሳይያቱ ይህን አይተው ለምን አትተያትም ለምን ትታገሻታለሽ? አሏት፡፡ እሷም ምን አደረገችኝ? ምን አጠፋች? አለቻቸው፤ ባንች ላይ የምትናገረውን ክፉ ቃል ሁሉ አትሰሚምን? አሏት እሷም መልሳ እኔስ ክፉ ግብሯን ባየሁ ጊዜ ከሰይጣን እንጅ ከእሷ እንዳልሆነ ስለማስብ በጠላቴ በሰይጣን እንጅ በእሷ ተቀይሜ አላውቅም ከረዳችሁኝ ጠላቴ ሰይጣንን እንዳባርረው እርዱኝ ብላ ለእህቶቿ መነኮሳት መለሰችላቸው፡፡
አንተም እንዲህ በል! ትናንት ክፉ ነገር የተናገረችኝ ክፉውን ሁሉ ያደረገችብኝ እሷ ሳትሆን ጠላቴ ሰይጣን ነው በልና ሰይጣንን ተቀየመው እንጅ ሚስትህን አትቀየማት፤ ከቻልህ ሚስትህን ሳይሆን ባንተ ላይ መልካም ሕይወት እንዳይኖር ያደረገ ሰይጣንን አስወጥተህ ስደደው እንጅ ሚስትህን ለምን ትሰዳታለህ? ሚስትህን መፍታትን ካሰብህ መልካም ነገርን ለይተህ አታውቅም ማለት ነው፤ ‹‹ያገባ መልካም ነገርን አደረገ›› ብሎ መምህርህ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሮልህ እንዴት ‹‹እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር መፋታትን እጠላለሁ›› ሚል 2፥16 ወደ ተባለው የተጠላ ተግባር ትመለሳለህ? አስተውል! ባንተና በእሷ መካከል ያለው ክፉ ነገር ሁሉ አንተም እሷም ሳታውቁ ጠላት ሰይጣን የሠራው ነው እንጅ አንተም እሷም ይህን አላደረጋችሁትም፡፡
ሁለት መነኮሳት በበረሃ ይኖሩ ነበረ ብዙ ዘመናት ብቻቸውን በበረሃ ውስጥ በጥሩ ፍቅር ከቆዩ በኋላ መጣላት ጀመሩ የመጣላታቸው ምክንያቱ ደግሞ ያንደኛው መነኩሴ በትር መጥፋቷ ነው፤ ብቻቸውን እየኖሩ የሰው ፊት አይተው አያውቁም ማን ወሰደው ብለው ሲፈልጉ አጡት በትሩ የጠፋችበት መነኩሴ ለብዙ ዘመናት አብሮት የኖረ ወንድሙን ተቀየመው ካንተና ከእኔ በቀር በዚህ በረሃ ማን ይኖራል? ሰብረህ ጥለህብኝ ነው እንጅ ሌላ ማን ይወስደዋል? አለው እያደር ፍቅራቸው እየጠፋ መለያየታቸው እየሰፋ ሄደ በመጨረሻ በትሩ የጠፋበት መነኩሴ ተነሥቶ በቃ ካንተ ጋር መኖር ፈተና ሁኖብኛልና ተወኝ በዓቴን ለቅቄ ልወጣ ነው አንተ ኑርበት አለው ወንድሙም ከእግሩ ላይ ወድቆ ይቅርታ አድርግልኝ እኔ ይህን አላደረግሁትም በዓትህን ለቀህ አትሂድ እንዳስለመድነው አብረን በፍቅር እንኑር ብሎ ለመነው እሱ ግን እምቢ አለና ወጥቶ ሊሄድ ሲዘጋጅ እንዴት ወንድሜ በሰይጣን ፈተና በዓቱን ለቆ ሲሄድ ዝም እላለሁ ብሎ ተንበርክኮ ጸሎት አደረገ ያንጊዜ መልአኩ መጥቶ ይህን ያደረገው እርሱ አይደለም፤ ሰይጣን ይህን አደረገው ብሎ ያንን ሰይጣንን በእሳት ጅራፍ እየገረፈ የደበቀውን በትር እንዲያመጣ አዘዘው ሰይጣንም እየቀባጠረ በትሩን ወርውሮላቸው ሄደ እነሱም እንደ ቀደመው ሁነው በፍቅር መኖር ጀመሩ፡፡
ከዚህ ተማሩ ክፉ ነገርን ሁሉ እናንተ አላደረጋችሁትም ትናንት እጃችሁ ላይ የነበረው ምርኩዛችሁ የጠፋው በእናንተ አይደለም ሰይጣን ሲከታተላችሁ ኑሮ ይህን አደረገባችሁ፤ ስለጠፋው በትር ስትከራከሩ እጃችሁ ላይ ያለችውን መንግሥተ ሰማያትን ለምን ታጣላችሁ?
ወንድሜ ትዳር መልካም ነው በል!
2.    ትዳር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው
ይቀጥላል…..

Saturday, 30 November 2019


      የእግዚአብሔር ማደሪያ
‹‹ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ ነፍሴ አትፀየፋችሁም በመካከላችሁም እሄዳለሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛችሁ›› ዘሌ 26፥11 ‹‹የምስክሩ ድንኳን፣ የመገናኛ ድንኳን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ›› የሚለው ሦስቱም ስያሜ የተሰጠው ሙሴ ያዘጋጀው ድንኳን ነው፡፡ ዘፀ 29፥42፣ ዘኁ 17፥7፡፡
ይህ ድንኳን ጠቅላላ ስፋቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን ሃያው ክንድ ቅድስት፣ አሥሩ ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን ይባላል፡፡ በሃያው ክንድ ካህናት ዘወትር አገልግሎታቸውን ይፈጽሙበታል፤ በአሥሩ ክንድ ግን ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ጊዜ ዕለተ ዮሴፍ የሚባል አላቸው በጥቅምት ጨረቃ በአሥረኛው ሠርቅ የሚከበር ነው በዚያ ቀን መሥዋዕት የሚሠዋው ሊቀ ካህናት ብቻ ይገባባታል እንጅ ማንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ‹‹ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በኋለኛይቱ ድንኳን ግን ሊቀ ካህናት ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል›› ዕብ 9፥6-7 እንዲል፡፡
በቅድስቱ ውስጥ መቅረዙ፣ መሠዊያው፣ መሥዋዕቱ ይገኝባታል በቅድስተ ቅዱሳኑ ደግሞ ማዕጠንተ ወርቅ፣ ጽላቱ፣ መሶበ ወርቅ፣ በትረ አሮን ይገኛሉ፡፡
-       መቅረዙ በሠርክ ይበራል በማለዳ ይጠፋል ስድስት የፈትል ማስቀመጫ (ምንባረ ፈትል) በሁለቱ ጎን ነበረው፤ በስድስቱ የፈትል ማስቀመጫዎች መካከል ያለ ሥረ ወጥ የፈትል ማስቀመጫ አለ ካህኑ ዘይቱን የሚጨምረው በመካከል ባለው በሥረ ወጡ ነው፤ ከላይ እስከታች ያሉት አዕፁቅ (የፈትል ማስቀመጫዎች) ዘይት የሚያገኙት ከዚህ ከመካከለኛው (ከሰባተኛው የፈትል ማስቀመጫ) ነው ማለት ነው፡፡ በአፍኒንና በፊንሐስ ዘመነ ክህነት ካልሆነ በቀር በዚህ መቅረዝ ላይ መብራት በሌሊት ተለይቶት አያውቅም፡፡
-      መሠዊያውና መሥዋዕቱም (ሰደቃ) የሠርክና የነግህ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ነው፡፡ በቅድስቱ ውስጥ መሆኑም ስለዚህ ነው በየቀኑ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስለሆነ፡፡ ባዶ አይሆንም የነግሁን በልተው የማታ መሥዋዕት ሠውተውበት ይሄዳሉ፡፡ አሥራ ሁለት ሕብስተ ገጽ ነው በቀን የሚያቀርቡት፡፡ ስድስቱን ማለዳ ያቀርቡታል ስድስቱን ለማታ መሥዋዕት አዘጋጅተው ይሄዳሉ እንጅ ሰደቃው ባዶ አይሆንም ነበር፡፡
-      ማዕጠንተ ወርቁ እና የዕጣን መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይገኛሉ ሊቀ ካህናቱ በዓመት ሲገባ የዕጣን መሥዋዕት የሚያቀርብባቸው ናቸው፤ ካህኑ ዘካርያስ ቅዱስ ገብርኤልን ያየው በዚህ መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ነው ሉቃ 1፥11
-      ሁለንተናዋ በወርቅ የተለበጠችው ታቦት በእርሷም ላይ ሙሴ የሳላቸው ኪሩቤል እንዲሁም መለወጥ የሌለበት የእስራኤል መና ያለባት መሶበ ወርቅ እና የአሮን የካህንነቱ ምስክር የሆነችው የአሮን በትር በዚህ ቅዱስ ክፍል ይገኛሉ፡፡
·       የወርቁ መሠዊያ መሥዋዕቱ ይቀርብበታል፣
·        በታቦቱ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝበታል፤
·        በትረ አሮንና በመሶበ ወርቁ ምልክቶች ናቸው፡፡ ሳይተክሏት የምታፈራዋ ውኃ ሳያጠጧት የምታፈራዋ የአሮን በትር ያለ ዘርዓብእሲ በድንግልና ፀንሳ የምትወልደውን እመቤታችንን ትሰብካለች መሶበ ወርቁም ዘመን ሳይሰፈርለት የሚኖረውን አማናዊውን መሥዋዕታችንን ክርስቶስን ያመለክታል፡፡
የመገናኛው ድንኳን በስተምሥራቅ በኩል የሚገኝ አንድ በር ነበራት፤ እንግዲህ ስንቱን እነግራችኋለሁ ምሰሶወቿን፣ መጋረጃዋን፣ ቁልፎቿን፣ ከሐር መጋረጃ እንዲሠራ የታዘዘውን አጥሯን፣ ካስማዎቿን አውታሯን ስንቱን አነሣዋለሁ፡፡ እንዲሁ መንገደኛ ነኝና የቀናኝን እያነሣሣሁ አልፋለሁ፡፡ እናንተ ግን በቦታው ተገኝታችሁ ብትጎበኙት መልካም ነው ከዘፀ 25 እስከ ዘፀ 40 ድረስ በሰፊው ተመዝግቧል፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከተበተኑበት መሰብሰብ፣ ከባርነት ቤት ወደ ነጻነት፣ ከስደት ወደ ርስት በመለሰበት ወቅት ሕዝቡ እርሱን የሚያገኙበት፤ እርሱም ሕዝቡን የሚያገኝበት መገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው ‹‹በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስ ሥሩልኝ›› ዘፀ 25፥8 ከከብሩ የተነሣ ሰማይ ማደሪያው ይሆን ዘንድ አይችልም ነገር ግን በሰው ፍቅር ምክንያት የሚያድርበት ድንኳን እንዲያዘጋጁለት እስራኤልን አዘዛቸው፤ ይህ ፍቅር ታላቅ ነው፤ በሰማይ ዙፋኑን የዘረጋ እግዚአብሔር በስደተኛ ሕዝብ መካከል ሊያድር መቅደስ አስገነባ ያን ጊዜ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ ሁለት ዓመት ሆኗቸው ነበረ፤ በምድረ በዳ ላለ ሕዝብ ከዚህ የሚበልጥ ምን ደስታ አለ? ለአራት መቶ ዓመት በገነቡት ከተማ ውስጥ እግዚአብሔር መቅደስ እንዲገነቡለት አላዘዛቸውም ነበር ከተማው ለእርሱ ማደሪያ የሚሆን አልነበረምና ምድረ በዳውን መረጠ፡፡
የሕዝቡስ ነገር አይገርማችሁም? ይሄ ስደተኛ ሕዝብ ያለውን ሁሉ አምጣ ተብሎ ሲጠየቅ ምንም አልከለከለም ሁሉን ሰጠ ወርቅ፣ ብር፣ ነሐስ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ ግምጃ፣ የበፍታ መጋረጃ ሌሎችም ማንም በልቡ ያሰበውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ይሠራበት ዘንድ አመጣ እንጅ በመንገድ ሳለሁ ምን አለኝ? አላለም፡፡ ለሚሠራው ሰው ለሙሴም ድንኳኑን በሰማያዊው ድንኳን አምሳል እንዲያዘጋጀው ወደ ደብረ ሲና ወስዶ ለአርባ ቀናት ሰማያዊውን ድንኳን አስጎበኘው ከብርሃን የተሠራውን፣ የእሳት መጋረጃ ያለውን፣ የውኃ መርገፍ፣ የእሳት ክዳን ያለውን፣ በመብረቅ የታጠረውን ሰማያዊ ማደሪያውን አሳየው፡፡ በዚያው አምሳል በምድር ያለውን ማደሪያውን ይሠራለት ዘንድ አዘዘው፤ ቅዱስ ያሬድ ይህን ድንኳን የሰማይ ሁለተኛ ያደርገዋል ‹‹ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለቅድስት ደብተራ፤ የጽዮን በኵር አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ሁለተኛም ልዩ የሆነች ድንኳኑን እንዴት እንዴት እንደሚሠራት ለሙሴ አሳየው›› ብሎ በዜማ ይቀኛል፡፡ 
አሠራሯ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ ሥራዋ ግን በምድራውያን ሰዎች እጅ የተፈጸመ ይህች የመገናኛ ድንኳን እመቤታችን ናት፤ በሰዎች መካከል ያለች ቤተ መቅደሱ ሰባት የእሳት መጋረጃ ያላት፣ ፊቷ ወደ ምሥራቅ የዞረ፣ አንድ ክርስቶስ ብቻ የሚገባባት አንድ በር ያላት፣ ያውም ሕዝቅኤል እንዳየው ለዘለዓለም ታትሞ የሚኖር በር ሕዝ 44፥1 ማዕጠንተ ወርቁ፣ መሶበ ወርቁ፣ መቅረዙ፣ ማዕዱ ሰባቱ ንዋያት የሚገኙባት በሠርክም በነግህም መሥዋዕት የማይታጎልባት አማናዊት ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ናት፡፡
ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጀርባዋን ለምዕራብ አድርጎ መሥራቱ እመቤታችን ከምሥራቅ ይመጣል ዕን 3፥3 ተብሎ የተነገረውን መሢህ የምትጠብቅ ሲኦል ገሐነም የማይቀበላት ለአንድ ሊቀ ካህናት መግቢያ የተዘጋጀች ባለ አንድ በር ቤተ መቅደስ መሆኗን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ሁሉ እግዚአብሔርን በክብር ተገልጦ የሚያዩት ከደብረ ሲና በኋላ በዚህ መገናኛ ድንኳን ነበረ፤ ጠላት የበረታበት የሚያመልጥባት፣ ብርቱ ጠላት የሚሸነፍባት ይህች ድንኳን ምዕመናን አጋንንትን ድል የነሡባት አጋንንትም ድል የተነሡባትን አማናዊቷን የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን እመቤታችንን ያመለክተናል፡፡ ዘኁ 16፥42
እግዚአብሔር ስደተኛውን ሕዝብ የገነባውን ከተማ የሠራውን ቤት አስጥሎታልና የመጀመሪያውን ቤቱንም አፍርሶበታልና ሌላ አዲስ ቤት በሰማያዊው ቤተ እግዚአብሔር አምሳል ሠራላቸው፤ ይገርማል! ከፈርዖን ጋር ከመኖር ከእግዚአብሔር ወደ መኖር፣ ከግብጻውያን ጋር ከማደር ከኪሩቤል ጋር ወደ መነጋገር፣ ‹‹ሂዱ ጡብ እርገጡ፣ ሥሩ ከጡቡ ቁጥር ምንም አያጎሉላችሁም፣ጭድም አይሰጧችሁም›› ዘፀ 5፥18 ከሚለው ክፉ ድምጽ ለይቶ ከሥርየት መክደኛው የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ወደ መስማት መለሳቸው፡፡
በእርግጥ ሕዝቡ ይህ ሁሉ ቢሆንላቸውም ወደ ጣዖት ወደ ኃጢአት ማዘንበላቸው አልቀረም ለእግዚአብሔር መባውን ልባቸው እንደ ፈቀደ ያመጡትን ያክል ለጣዖቱም ሥራ በእጃቸው በጣታቸው እና በጆሯቸውም ያለውን ጌጣቸውን ማምጣታቸው አልቀረም፤ ዘፀ 32፥2 በእግዚአብሔር ማደሪያ ዙሪያ ሰፍረው እየኖሩ ሞት እየነጠቀ ጨረሳቸው ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ መንገዱን የሞት መንገድ አደረጉት፤ የተስፋይቱን ምድር የሚወርሰውን ትውልድ በመንገድ አዘገዩት፡፡
በመጨረሻም፡- ይህ ድንኳን በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ገባ፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ውስጥ ድንኳን ሥሩልኝ አላለም መላዋ ኢትዮጵያ ድንኳኑ ናትና፡፡ እስራኤልን በደጅ ጽናቷ ያሸነፈችው ሙሽራዋ ኢትዮጵያ በመጨረሻ የእስራኤልን ክብር ከእስራኤል ቀምታ ወሰደች፤ እስራኤል የማይገባት ስለሆነ ብኵርናዋን ለኢትዮጵያ ለቀቀች፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ማደሪያው መሆኗን ይታወቅ ዘንድ በመናገሻዋ ከተማ አክሱም ገብቶ የነገሠበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ ንጉሥ ማደሪያ፡፡ የአክሱም የሕንደኬ ንግሥታት፣ እነ አቤሜሌክም ለደጅ ጥናታችን ማረጋገጫ ናቸው፡፡  1ነገ 10፥1፣ ሥራ 8፥27፣ ተረፈ ኤር. 8፥8 ለዚህ ነው ዛሬ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
Ø ታቦት
Ø በእስራኤል ምድር የሚገኙ በኵሮች ሁሉ
Ø ሌዋውያኑ ዛሬ ወደ ሀገራችን መናገሻ ከተማ አክሱም የገቡበት ቀን ነው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሕገ ኦሪት ተሸጋገርን ወደ ክርስቶስ መርታ የምታደርሰንን ቅድስት ኦሪትን የተቀበልን ዛሬ ነው፤ በወርቅ የተለበጠውን ጽላት ከነ ሌዋውያኑ ኦሪቱን ከነ መተርጉማኑ ተሰጠን፡፡ የብሉይ ኪዳን ድኅነት ለሁሉ መሆን አይችልምና እኛ ቅዱሳት ንዋያቱን ስንቀበል እስራኤል ባዶ ሆነች፡፡ ግብጻውያን በኃይለ እግዚአብሔር ተረትተው በኵሮቻቸውን አጡ፤ እስራኤል በሃይማኖት ድል ተነሥታ በኵሮቿን ለኢትዮጵያ ሰጠች፡፡ ከዛሬ ጀምሮ የሰሎሞን በኩር ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ ይነግሣል፡፡ እግዚአብሔር የማለላት የዳዊት ዙፋን በኋላም የእግዚአብሔር ልጅ የወረሳት የዳዊት ምንግሥት በኢትዮጵያ ተዘረጋች፡፡ መዝ 131፥11

Friday, 29 November 2019


የነፍሴ ጥያቄ ፫
በትዳር ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዴት ይቻላል?
በዚህ ዐምድ ሥር አስቀድሜ እንደተናገርሁት አስቀድሞ በኔ ዘንድ ያለውን የነፍሴን ጥያቄ መመለስ አስቤ የጀመርሁት ሲሆን ከእኔም በተጨማሪ የብዙ ነፍሳትን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመልስበት ዐምድ ነው፡፡
ለዛሬ ከተላኩልኝ ጥያቄዎች መካከል ይህን መረጥሁት፡፡ እግዚአብሔር በረድኤት አይለየን፡፡
አባታችን አዳም ለመጀመሪያ ጊዜ የጠየቀው ጥያቄ ቢኖር የሚረዳው ጓደኛ ለማግኘት ነው፡፡ ዓለምን እና በውስጧ ያለውን ሁሉ ያለ ንፍገት በልግስና ለሰው ልጆች አባት አዳም የሰጠው ጌታ ዘፍ 1፥28 የሚረዳው እንደ እርሱ ያለ ረዳት ሳይሰጠው ለአንድ ሱባኤ ያክል ዘግይቶበታል፡፡ ሔዋንን ለአዳም ማስገኘት ሰማይና ምድርን አሳምሮ ፈጥሮ ለአዳም ከመስጠት የሚበልጥ ሆኖ አይደለም፤ አዳም በገዛ ፈቃዱ ሔዋንን ጠይቆ ከሥላሴ ይቀበል ዘንድ ስለሚገባ ነው እንጅ፡፡
የእግዚአብሔር ዝምታ በአዳም ሕይወት ውስጥ የታየው በሔዋን ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ሳይጠይቀው አርዓያውን መልኩን ሰጥቶ ፈጠረው፣ ሳይለምነው በፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው፣ ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ስም እንዲያወጣ አሠለጠነው ዘፍ 2፥19 ነገር ግን ሔዋንን ሳይሰጠው ብቻውን አዘገየው መልአካዊ ባሕርይ ያለው ፍጥረት በመሆኑ እንደ እንስሳት ሲፈጠር ጀምሮ የሴት ጓደኛ አልተሰጠችውም እስከ ሰባተኛው ቀን መጨረሻ ድረስ ዝም ብሎታል፤ ከዚህ በኋላ ግን አዳም ለእንስሳት ስም ባወጣበት ጊዜ ሁለት፣ ሁለት ሁነው ቢያያቸው ‹‹እኔን ብቻ ያለ ረዳት ለምን ፈጠርኸኝ›› ብሎ ጠየቀ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ የተባለው ቃል ከዚህ በኋላ ነው የሚመጣው ‹‹ለአዳምሰ ኢተረክበ ሎቱ ረድኤት ዘከማሁ ንግበር ሎቱ ቢፀ ዘይረድኦ፤ ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም የሚረዳው ጓደኛ እንፍጠርለት›› ዘፍ 2፥21 የሚለውን ቃል እግዚአብሔር ተናገረ፡፡ በዚህ ቃል መሠረት በአርዓያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው ሰው እርሱን የምትመስል ሴት ከጎኑ ፈጠረለት፡፡
ገነትን ጫጉላ ቤት፣ እግዚአብሔርን አባት፣ ቅዱሳን መላእክትን እንደ ዘመድ ወዳጅ አድርገው በቅድስት ምድር በገነት ውስጥ ኖሩ፡፡
ትዳር በሰው ልጅ ፈቃድ፣ በእግዚአብሔር ፈጻሚነት የተጀመረ ሲሆን
·       በገነት ውስጥ ሆኖ
·       በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ
·       በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ተከቦ ባለበት ሰዓት ፈተና ሊያጋጥመው ይችል ይሆን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ አወ እውነት ነው የሚል ይሆናል፡፡
አዳምና ሔዋን ጠብና ክርክርን ሳያውቁ የኖሩት በሰባቱ ዓመታት ብቻ ነው ከዚያ በኋላ ኃጢአት ወደ ሰው ባሕርይ ሲገባ መለያየት ይጀምራሉ፡፡ የሞትን ዛፍ ስለመብላቱ ሲጠየቅ ‹‹ካንተ ጋር ትሁን ብለህ የሰጠኸኝ ሴት ሰጠችኝና በላሁ›› ዘፍ 3፥12 አለ፡፡ ጠብ በዚህ ጊዜ ተጀምሯል፤ ‹‹ይህች አጥንት ካጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋየ ናት እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› ዘፍ 2፥23 ብሎ ወደ ራሱ ያቀረባት፣ ስለ እርሷ እናትና አባትን ሌላውንም ሁሉ ትቶ እንደሚከተላት የተነገረላት የአዳም ምትክ (ሴት) ኃጢአትን ባወቀ ሰው ዘንድ ሞገስን አላገኘችም፡፡
በእርግጥም ከተፈጠረ ቀን ጀምሮ እሷ እስከተገኘችበት ቀን ድረስ አንቀላፋ ተብሎ ያልተነገረለት አዳም ለእሷ ሲል አንቀላፋ፣ ከአጥንቱ ተከፍላ እንደተፈጠረች ቢያውቅም ወደዳት እንጅ አልጠላትም፣ ዕራቁቱን ሆኖ ሲቀርባት የማያፍራት ዕራቁቷን ሆና ስትቀርበው የማይጠላት ባሏ አልነበረምን? ስለምን እንዲህ ያለ መከራን አመጣችበት? እሱ ሰው ለመሆን ምክንያት ቢሆናት እሷ ለመሞት ምክንያት ሆነችው፤ እሱ ወደ ገነት ቀድሞ ገብቶ አስገባት እሷ ከገነት አስወጣችው፡፡
ይህ በሆነ ጊዜ ዝም የሚል አዳም ማግኘት እንደምን ይቻላል? ኃጢአትንስ ያወቀ ሰው በደልን ሁሉ ሽሮ ሰዉን መውደድ እንዴት ይችላል? እግዚአብሔር በፈጠረው ትዳር ውስጥ እግዚአብሔር ያልፈጠራቸው ችግሮች ሲፈጠሩ እንዴት እናልፋቸዋለን? የሰው ልጅ የገነባውን ለማፍረስ ዓለምን የከከበቧት አጋንንት ብዙ ናቸው ከእነዚህ አጋንንት ዐይን የተሰወረ ትዳር ማገኘት የሚቻለው እንዴት ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በመጻሕፍት ውስጥ ያሉ ብዙ ትዳሮችን ምስክር አድርገን በቀጣይ እናያቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

Thursday, 21 November 2019

 
ጠላቶቻችን ሆይ!
በሥጋ ወንድሞቻችን በወንጌል በኩል ግን ጠላቶቻችን ከሆኑ ሰዎች ጋር ለመኖር ልምድ ያለው እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማንም በዓለም ላይ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡ አባቶቻችን ጊዜ ቢያጋጥማቸው ሥልጣን ቢደላደልላቸው እንደ መንግሥት ያስገብሩ ይሆናል እንጅ ማንንም በሃይማኖት ምክንያት በደል አያደርሱም ነበር በእርግጥ ማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅብዓ መንግሥት አክብራ የሾመችው እንደ መሆኑ ክርስቲያናዊ መንግሥት በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ የጎሣ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ክርስቲያን የመሆን አዝማሚያ ይታይባቸው ነበር ነገር ግን በራሳቸው ፈቃድ እንጅ ማንም አስገድዶ ክርስቲያን አላደረጋቸውም፡፡
ምን አልባትም በሃይማኖት ምክንያት ቁጥጥር ተደርጎ ከሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አባ ጅፋር ባሉ አክራሪ እስላሞች የተደረገው ነው እሚሆነው፡፡ አባ ጅፋር ጅማን በሙሉ እስላም ለማድረግ ቋንቋዋንም አረበኛ ለማድረግ ይሠሩ ነበር ይባላል ያንጊዜ ዓጼ ምኒልክ ሰምተው ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደ ጻፉላቸው ጳውሎስ ኞኞ ጽፏል፡፡ የሐረር ሡልጣኖችም ከዓጼ ምኒልክ ጋር ጦርነት የመክፈታቸው ምክንያት እስላም በመሆናቸው ሳይሆን ማዕከላዊው መንግሥትም እስላም ካልሆነ አንገብርም በማለታቸው እንደሆነ ተጽፏል፡፡ እንዲያውም ግብር እንዲያስገቡ ወታደሮች ሲላኩ የእስላም ቆብና ጀለብያ ለዓጼ ምኒልክ ልከውላቸዋል ይባላል፡፡
ይህ በመሆኑ ምክንያት ካልሆነ ከጠላት ጋር ሀሳቡን አክብሮ በመኖር ከእኛ ጋር የሚተካከል ታሪክ ያለው ሰው ማነው? ከዛሬ በቀር በወንጌል ካልሆነ በሥጋ ጠላት ኖሮብን አያውቅም ነበር፤ ዛሬ ግን በወንጌል ብቻ ሳይሆን በሥጋም ጠላቶቻችን በዙ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መከራን እየተቀበሉ ነው፡፡
ሲገድሉንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከነገሥታቱ ጋር ሆና እንደ በደለቻቸው ሲናገሩ ይሰማል፤ ነገር ግን ታሪክ ባለማወቃቸው ይስታሉ እንጅ  ታሪካችን እንደዚያ አያሳይም፡፡ እስላም ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እኛኮ በመንግሥት ደረጃ ተዋቅረናል፤ የኢትዮጵያ ክርስትና እንደ ሌሎቹ ሀገራት በሕዝባዊ ቤት የተጀመረ አይደለም በነገሥታት ቤተ መንግሥት ተጀምሮ እየተስፋፋ የመጣ ነው እንጅ፡፡ ያንጊዜ ነገሥታቱ ያለ ምክረ ካህን በኢትዮጵያ ላይ እንዲቀመጡ ሚፈቅድላቸው ይመስላቸዋል? አጼ ገላውዴዎስ የፖርቹጋልን ወታደሮች አስወጥተው የሰደዷቸው እኮ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስላልፈቀዱ ነው እንጅ የቤተ መንግሥቱ መሳፍንት ጋር ተማክረው አልነበረም፡፡
አናሲሞስ ነሲቡንስ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ያደረገው ማን ነው? በወቅቱ ከዓጼ ምኒልክ የፈቃድ ደብዳቤ እንዲሰጠው እና ወደ ወለጋ ሂዶ ወንጌል እንዲሰብክ መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ አሳትሞ እንዲያሰራጭ ያደረገው ማነው? ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ፕሮቴስታንት በኢትዮጵያ መኖሩ ያጠራጥር ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ለክፉዎችም ለዳጋጎችም ነፍስን አሳልፎ መስጠትን እንጅ በክፉ ዓለም ውስጥ ከደጋጎቹ ጋር ብቻ መኖርን አታስተምርም፡፡   
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ከአባታችሁ ሰይጣን የተማራችሁትን መግደል ማስቆም ባንችልም እናንተም ሃይማኖታችንን ማስቆም አትችሉም፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ስለክርስቶስ መሞትን አባቶቻችን ሐዋርያት አስተምረውናል፤ አምኖ መሞት እንጅ ሃይማኖትን ክዶ በሕይወት መኖር በእኛ ዘንድ ሕይወት አይደለም፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ስታሳድዱን ያንጊዜ ዝም የምንለው ከፊታችን ያለው ክርስቶስ ‹‹ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ ደስ ይበላችሁ በሰማይ ዋጋችሁ ታላቅ ነውና›› ማቴ 5፥10 እያለ ስለሚያጽናናን ነው፡፡
Ø  ጠላቶቻን ሆይ! ቤታችንን ንብረታችንን ስታቃጥሉ ዝም ያልነው ‹‹በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና ብሎ ያስተማረን መለኮታዊ ቃል ስላለን እሱ ትዝ እያለን ነው፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! እናንተ መንገድ ላይ ወጥታችሁ ስትዘፍኑ እኛ ኀዘን የተቀመጥነው፤ እናንተ መንገድ ለመዝጋት ስትሰለፉ እኛ ለምኅላ የቆምነው ‹‹ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና›› ስለሚል ነው፡፡ ኃጢአት ሠርቶ ከመደሰት ስለ ክርስቶስ መከራ እየተቀበሉ ማዘን ይበልጣልና፡፡   
Ø  የአብርሃም አምላክ ካራንን ልቀቁ ሲል የተሻለች ከነዓንን ለአብርሃም አዘጋጅቶ ነው፤ አትጠራጠሩ እናንተ ሣራን ለራሳችሁ ለማድረግ ስትሮጡ እግዚአብሔር አጋርን ሳይቀር ከእጃችሁ ነጥቆ ለአብርሃም ያደርጋታል፡፡
Ø  እናንት ሰነፎች ሆይ! ኢትዮጵያ እንደ ሣራ ናት፤ የነቢይ ሚስት ናትና ንጉሥ አያገባትም፡፡ ውበቷ አስክሯችሁ ደም ግባቷ አስቷችሁ ክፉ ባታደርጉ መልካም ነው፤ ኢትዮጵያ የንጉሡ ናት፡፡ በእናንተ ፊት አንገቱን የደፋው አብርሃም ካልጸለየላችሁ የማትድኑበት ወራት ይመጣልና አብዝታችሁ አትበድሉ፡፡