የነፍሴ ጥያቄ ፫
በትዳር ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዴት ይቻላል?
በዚህ ዐምድ ሥር አስቀድሜ እንደተናገርሁት
አስቀድሞ በኔ ዘንድ ያለውን የነፍሴን ጥያቄ መመለስ አስቤ የጀመርሁት ሲሆን ከእኔም በተጨማሪ የብዙ ነፍሳትን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን
የምትመልስበት ዐምድ ነው፡፡
ለዛሬ ከተላኩልኝ ጥያቄዎች መካከል
ይህን መረጥሁት፡፡ እግዚአብሔር በረድኤት አይለየን፡፡
አባታችን አዳም ለመጀመሪያ ጊዜ
የጠየቀው ጥያቄ ቢኖር የሚረዳው ጓደኛ ለማግኘት ነው፡፡ ዓለምን እና በውስጧ ያለውን ሁሉ ያለ ንፍገት በልግስና ለሰው ልጆች አባት
አዳም የሰጠው ጌታ ዘፍ 1፥28 የሚረዳው እንደ እርሱ ያለ ረዳት ሳይሰጠው ለአንድ ሱባኤ ያክል ዘግይቶበታል፡፡ ሔዋንን ለአዳም
ማስገኘት ሰማይና ምድርን አሳምሮ ፈጥሮ ለአዳም ከመስጠት የሚበልጥ ሆኖ አይደለም፤ አዳም በገዛ ፈቃዱ ሔዋንን ጠይቆ ከሥላሴ ይቀበል
ዘንድ ስለሚገባ ነው እንጅ፡፡
የእግዚአብሔር ዝምታ በአዳም
ሕይወት ውስጥ የታየው በሔዋን ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ሳይጠይቀው አርዓያውን መልኩን ሰጥቶ ፈጠረው፣ ሳይለምነው በፍጥረት ሁሉ ላይ
ሾመው፣ ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ስም እንዲያወጣ አሠለጠነው ዘፍ 2፥19 ነገር ግን ሔዋንን ሳይሰጠው ብቻውን አዘገየው መልአካዊ ባሕርይ
ያለው ፍጥረት በመሆኑ እንደ እንስሳት ሲፈጠር ጀምሮ የሴት ጓደኛ አልተሰጠችውም እስከ ሰባተኛው ቀን መጨረሻ ድረስ ዝም ብሎታል፤
ከዚህ በኋላ ግን አዳም ለእንስሳት ስም ባወጣበት ጊዜ ሁለት፣ ሁለት ሁነው ቢያያቸው ‹‹እኔን ብቻ ያለ ረዳት ለምን ፈጠርኸኝ››
ብሎ ጠየቀ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ የተባለው ቃል ከዚህ በኋላ ነው የሚመጣው ‹‹ለአዳምሰ ኢተረክበ ሎቱ ረድኤት ዘከማሁ ንግበር ሎቱ
ቢፀ ዘይረድኦ፤ ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም የሚረዳው ጓደኛ እንፍጠርለት›› ዘፍ 2፥21 የሚለውን ቃል እግዚአብሔር
ተናገረ፡፡ በዚህ ቃል መሠረት በአርዓያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው ሰው እርሱን የምትመስል ሴት ከጎኑ ፈጠረለት፡፡
ገነትን ጫጉላ ቤት፣ እግዚአብሔርን
አባት፣ ቅዱሳን መላእክትን እንደ ዘመድ ወዳጅ አድርገው በቅድስት ምድር በገነት ውስጥ ኖሩ፡፡
ትዳር በሰው ልጅ ፈቃድ፣ በእግዚአብሔር
ፈጻሚነት የተጀመረ ሲሆን
·
በገነት ውስጥ ሆኖ
·
በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ
·
በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ተከቦ ባለበት ሰዓት ፈተና ሊያጋጥመው
ይችል ይሆን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ አወ እውነት ነው የሚል ይሆናል፡፡
አዳምና ሔዋን ጠብና ክርክርን
ሳያውቁ የኖሩት በሰባቱ ዓመታት ብቻ ነው ከዚያ በኋላ ኃጢአት ወደ ሰው ባሕርይ ሲገባ መለያየት ይጀምራሉ፡፡ የሞትን ዛፍ ስለመብላቱ
ሲጠየቅ ‹‹ካንተ ጋር ትሁን ብለህ የሰጠኸኝ ሴት ሰጠችኝና በላሁ›› ዘፍ 3፥12 አለ፡፡ ጠብ በዚህ ጊዜ ተጀምሯል፤ ‹‹ይህች አጥንት
ካጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋየ ናት እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› ዘፍ 2፥23 ብሎ ወደ ራሱ ያቀረባት፣ ስለ እርሷ እናትና
አባትን ሌላውንም ሁሉ ትቶ እንደሚከተላት የተነገረላት የአዳም ምትክ (ሴት) ኃጢአትን ባወቀ ሰው ዘንድ ሞገስን አላገኘችም፡፡
በእርግጥም ከተፈጠረ ቀን ጀምሮ
እሷ እስከተገኘችበት ቀን ድረስ አንቀላፋ ተብሎ ያልተነገረለት አዳም ለእሷ ሲል አንቀላፋ፣ ከአጥንቱ ተከፍላ እንደተፈጠረች ቢያውቅም
ወደዳት እንጅ አልጠላትም፣ ዕራቁቱን ሆኖ ሲቀርባት የማያፍራት ዕራቁቷን ሆና ስትቀርበው የማይጠላት ባሏ አልነበረምን? ስለምን እንዲህ
ያለ መከራን አመጣችበት? እሱ ሰው ለመሆን ምክንያት ቢሆናት እሷ ለመሞት ምክንያት ሆነችው፤ እሱ ወደ ገነት ቀድሞ ገብቶ አስገባት
እሷ ከገነት አስወጣችው፡፡
ይህ በሆነ ጊዜ ዝም የሚል አዳም
ማግኘት እንደምን ይቻላል? ኃጢአትንስ ያወቀ ሰው በደልን ሁሉ ሽሮ ሰዉን መውደድ እንዴት ይችላል? እግዚአብሔር በፈጠረው ትዳር
ውስጥ እግዚአብሔር ያልፈጠራቸው ችግሮች ሲፈጠሩ እንዴት እናልፋቸዋለን? የሰው ልጅ የገነባውን ለማፍረስ ዓለምን የከከበቧት አጋንንት
ብዙ ናቸው ከእነዚህ አጋንንት ዐይን የተሰወረ ትዳር ማገኘት የሚቻለው እንዴት ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በመጻሕፍት
ውስጥ ያሉ ብዙ ትዳሮችን ምስክር አድርገን በቀጣይ እናያቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር አይለየን፡፡
No comments:
Post a Comment