>

Saturday, 30 November 2019


      የእግዚአብሔር ማደሪያ
‹‹ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ ነፍሴ አትፀየፋችሁም በመካከላችሁም እሄዳለሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛችሁ›› ዘሌ 26፥11 ‹‹የምስክሩ ድንኳን፣ የመገናኛ ድንኳን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ›› የሚለው ሦስቱም ስያሜ የተሰጠው ሙሴ ያዘጋጀው ድንኳን ነው፡፡ ዘፀ 29፥42፣ ዘኁ 17፥7፡፡
ይህ ድንኳን ጠቅላላ ስፋቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን ሃያው ክንድ ቅድስት፣ አሥሩ ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን ይባላል፡፡ በሃያው ክንድ ካህናት ዘወትር አገልግሎታቸውን ይፈጽሙበታል፤ በአሥሩ ክንድ ግን ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ጊዜ ዕለተ ዮሴፍ የሚባል አላቸው በጥቅምት ጨረቃ በአሥረኛው ሠርቅ የሚከበር ነው በዚያ ቀን መሥዋዕት የሚሠዋው ሊቀ ካህናት ብቻ ይገባባታል እንጅ ማንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ‹‹ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በኋለኛይቱ ድንኳን ግን ሊቀ ካህናት ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል›› ዕብ 9፥6-7 እንዲል፡፡
በቅድስቱ ውስጥ መቅረዙ፣ መሠዊያው፣ መሥዋዕቱ ይገኝባታል በቅድስተ ቅዱሳኑ ደግሞ ማዕጠንተ ወርቅ፣ ጽላቱ፣ መሶበ ወርቅ፣ በትረ አሮን ይገኛሉ፡፡
-       መቅረዙ በሠርክ ይበራል በማለዳ ይጠፋል ስድስት የፈትል ማስቀመጫ (ምንባረ ፈትል) በሁለቱ ጎን ነበረው፤ በስድስቱ የፈትል ማስቀመጫዎች መካከል ያለ ሥረ ወጥ የፈትል ማስቀመጫ አለ ካህኑ ዘይቱን የሚጨምረው በመካከል ባለው በሥረ ወጡ ነው፤ ከላይ እስከታች ያሉት አዕፁቅ (የፈትል ማስቀመጫዎች) ዘይት የሚያገኙት ከዚህ ከመካከለኛው (ከሰባተኛው የፈትል ማስቀመጫ) ነው ማለት ነው፡፡ በአፍኒንና በፊንሐስ ዘመነ ክህነት ካልሆነ በቀር በዚህ መቅረዝ ላይ መብራት በሌሊት ተለይቶት አያውቅም፡፡
-      መሠዊያውና መሥዋዕቱም (ሰደቃ) የሠርክና የነግህ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ነው፡፡ በቅድስቱ ውስጥ መሆኑም ስለዚህ ነው በየቀኑ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስለሆነ፡፡ ባዶ አይሆንም የነግሁን በልተው የማታ መሥዋዕት ሠውተውበት ይሄዳሉ፡፡ አሥራ ሁለት ሕብስተ ገጽ ነው በቀን የሚያቀርቡት፡፡ ስድስቱን ማለዳ ያቀርቡታል ስድስቱን ለማታ መሥዋዕት አዘጋጅተው ይሄዳሉ እንጅ ሰደቃው ባዶ አይሆንም ነበር፡፡
-      ማዕጠንተ ወርቁ እና የዕጣን መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ይገኛሉ ሊቀ ካህናቱ በዓመት ሲገባ የዕጣን መሥዋዕት የሚያቀርብባቸው ናቸው፤ ካህኑ ዘካርያስ ቅዱስ ገብርኤልን ያየው በዚህ መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ነው ሉቃ 1፥11
-      ሁለንተናዋ በወርቅ የተለበጠችው ታቦት በእርሷም ላይ ሙሴ የሳላቸው ኪሩቤል እንዲሁም መለወጥ የሌለበት የእስራኤል መና ያለባት መሶበ ወርቅ እና የአሮን የካህንነቱ ምስክር የሆነችው የአሮን በትር በዚህ ቅዱስ ክፍል ይገኛሉ፡፡
·       የወርቁ መሠዊያ መሥዋዕቱ ይቀርብበታል፣
·        በታቦቱ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝበታል፤
·        በትረ አሮንና በመሶበ ወርቁ ምልክቶች ናቸው፡፡ ሳይተክሏት የምታፈራዋ ውኃ ሳያጠጧት የምታፈራዋ የአሮን በትር ያለ ዘርዓብእሲ በድንግልና ፀንሳ የምትወልደውን እመቤታችንን ትሰብካለች መሶበ ወርቁም ዘመን ሳይሰፈርለት የሚኖረውን አማናዊውን መሥዋዕታችንን ክርስቶስን ያመለክታል፡፡
የመገናኛው ድንኳን በስተምሥራቅ በኩል የሚገኝ አንድ በር ነበራት፤ እንግዲህ ስንቱን እነግራችኋለሁ ምሰሶወቿን፣ መጋረጃዋን፣ ቁልፎቿን፣ ከሐር መጋረጃ እንዲሠራ የታዘዘውን አጥሯን፣ ካስማዎቿን አውታሯን ስንቱን አነሣዋለሁ፡፡ እንዲሁ መንገደኛ ነኝና የቀናኝን እያነሣሣሁ አልፋለሁ፡፡ እናንተ ግን በቦታው ተገኝታችሁ ብትጎበኙት መልካም ነው ከዘፀ 25 እስከ ዘፀ 40 ድረስ በሰፊው ተመዝግቧል፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከተበተኑበት መሰብሰብ፣ ከባርነት ቤት ወደ ነጻነት፣ ከስደት ወደ ርስት በመለሰበት ወቅት ሕዝቡ እርሱን የሚያገኙበት፤ እርሱም ሕዝቡን የሚያገኝበት መገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው ‹‹በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስ ሥሩልኝ›› ዘፀ 25፥8 ከከብሩ የተነሣ ሰማይ ማደሪያው ይሆን ዘንድ አይችልም ነገር ግን በሰው ፍቅር ምክንያት የሚያድርበት ድንኳን እንዲያዘጋጁለት እስራኤልን አዘዛቸው፤ ይህ ፍቅር ታላቅ ነው፤ በሰማይ ዙፋኑን የዘረጋ እግዚአብሔር በስደተኛ ሕዝብ መካከል ሊያድር መቅደስ አስገነባ ያን ጊዜ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ ሁለት ዓመት ሆኗቸው ነበረ፤ በምድረ በዳ ላለ ሕዝብ ከዚህ የሚበልጥ ምን ደስታ አለ? ለአራት መቶ ዓመት በገነቡት ከተማ ውስጥ እግዚአብሔር መቅደስ እንዲገነቡለት አላዘዛቸውም ነበር ከተማው ለእርሱ ማደሪያ የሚሆን አልነበረምና ምድረ በዳውን መረጠ፡፡
የሕዝቡስ ነገር አይገርማችሁም? ይሄ ስደተኛ ሕዝብ ያለውን ሁሉ አምጣ ተብሎ ሲጠየቅ ምንም አልከለከለም ሁሉን ሰጠ ወርቅ፣ ብር፣ ነሐስ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ ግምጃ፣ የበፍታ መጋረጃ ሌሎችም ማንም በልቡ ያሰበውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ይሠራበት ዘንድ አመጣ እንጅ በመንገድ ሳለሁ ምን አለኝ? አላለም፡፡ ለሚሠራው ሰው ለሙሴም ድንኳኑን በሰማያዊው ድንኳን አምሳል እንዲያዘጋጀው ወደ ደብረ ሲና ወስዶ ለአርባ ቀናት ሰማያዊውን ድንኳን አስጎበኘው ከብርሃን የተሠራውን፣ የእሳት መጋረጃ ያለውን፣ የውኃ መርገፍ፣ የእሳት ክዳን ያለውን፣ በመብረቅ የታጠረውን ሰማያዊ ማደሪያውን አሳየው፡፡ በዚያው አምሳል በምድር ያለውን ማደሪያውን ይሠራለት ዘንድ አዘዘው፤ ቅዱስ ያሬድ ይህን ድንኳን የሰማይ ሁለተኛ ያደርገዋል ‹‹ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለቅድስት ደብተራ፤ የጽዮን በኵር አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ሁለተኛም ልዩ የሆነች ድንኳኑን እንዴት እንዴት እንደሚሠራት ለሙሴ አሳየው›› ብሎ በዜማ ይቀኛል፡፡ 
አሠራሯ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ ሥራዋ ግን በምድራውያን ሰዎች እጅ የተፈጸመ ይህች የመገናኛ ድንኳን እመቤታችን ናት፤ በሰዎች መካከል ያለች ቤተ መቅደሱ ሰባት የእሳት መጋረጃ ያላት፣ ፊቷ ወደ ምሥራቅ የዞረ፣ አንድ ክርስቶስ ብቻ የሚገባባት አንድ በር ያላት፣ ያውም ሕዝቅኤል እንዳየው ለዘለዓለም ታትሞ የሚኖር በር ሕዝ 44፥1 ማዕጠንተ ወርቁ፣ መሶበ ወርቁ፣ መቅረዙ፣ ማዕዱ ሰባቱ ንዋያት የሚገኙባት በሠርክም በነግህም መሥዋዕት የማይታጎልባት አማናዊት ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ናት፡፡
ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጀርባዋን ለምዕራብ አድርጎ መሥራቱ እመቤታችን ከምሥራቅ ይመጣል ዕን 3፥3 ተብሎ የተነገረውን መሢህ የምትጠብቅ ሲኦል ገሐነም የማይቀበላት ለአንድ ሊቀ ካህናት መግቢያ የተዘጋጀች ባለ አንድ በር ቤተ መቅደስ መሆኗን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ሁሉ እግዚአብሔርን በክብር ተገልጦ የሚያዩት ከደብረ ሲና በኋላ በዚህ መገናኛ ድንኳን ነበረ፤ ጠላት የበረታበት የሚያመልጥባት፣ ብርቱ ጠላት የሚሸነፍባት ይህች ድንኳን ምዕመናን አጋንንትን ድል የነሡባት አጋንንትም ድል የተነሡባትን አማናዊቷን የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን እመቤታችንን ያመለክተናል፡፡ ዘኁ 16፥42
እግዚአብሔር ስደተኛውን ሕዝብ የገነባውን ከተማ የሠራውን ቤት አስጥሎታልና የመጀመሪያውን ቤቱንም አፍርሶበታልና ሌላ አዲስ ቤት በሰማያዊው ቤተ እግዚአብሔር አምሳል ሠራላቸው፤ ይገርማል! ከፈርዖን ጋር ከመኖር ከእግዚአብሔር ወደ መኖር፣ ከግብጻውያን ጋር ከማደር ከኪሩቤል ጋር ወደ መነጋገር፣ ‹‹ሂዱ ጡብ እርገጡ፣ ሥሩ ከጡቡ ቁጥር ምንም አያጎሉላችሁም፣ጭድም አይሰጧችሁም›› ዘፀ 5፥18 ከሚለው ክፉ ድምጽ ለይቶ ከሥርየት መክደኛው የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ወደ መስማት መለሳቸው፡፡
በእርግጥ ሕዝቡ ይህ ሁሉ ቢሆንላቸውም ወደ ጣዖት ወደ ኃጢአት ማዘንበላቸው አልቀረም ለእግዚአብሔር መባውን ልባቸው እንደ ፈቀደ ያመጡትን ያክል ለጣዖቱም ሥራ በእጃቸው በጣታቸው እና በጆሯቸውም ያለውን ጌጣቸውን ማምጣታቸው አልቀረም፤ ዘፀ 32፥2 በእግዚአብሔር ማደሪያ ዙሪያ ሰፍረው እየኖሩ ሞት እየነጠቀ ጨረሳቸው ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ መንገዱን የሞት መንገድ አደረጉት፤ የተስፋይቱን ምድር የሚወርሰውን ትውልድ በመንገድ አዘገዩት፡፡
በመጨረሻም፡- ይህ ድንኳን በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ገባ፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ውስጥ ድንኳን ሥሩልኝ አላለም መላዋ ኢትዮጵያ ድንኳኑ ናትና፡፡ እስራኤልን በደጅ ጽናቷ ያሸነፈችው ሙሽራዋ ኢትዮጵያ በመጨረሻ የእስራኤልን ክብር ከእስራኤል ቀምታ ወሰደች፤ እስራኤል የማይገባት ስለሆነ ብኵርናዋን ለኢትዮጵያ ለቀቀች፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ማደሪያው መሆኗን ይታወቅ ዘንድ በመናገሻዋ ከተማ አክሱም ገብቶ የነገሠበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ ንጉሥ ማደሪያ፡፡ የአክሱም የሕንደኬ ንግሥታት፣ እነ አቤሜሌክም ለደጅ ጥናታችን ማረጋገጫ ናቸው፡፡  1ነገ 10፥1፣ ሥራ 8፥27፣ ተረፈ ኤር. 8፥8 ለዚህ ነው ዛሬ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
Ø ታቦት
Ø በእስራኤል ምድር የሚገኙ በኵሮች ሁሉ
Ø ሌዋውያኑ ዛሬ ወደ ሀገራችን መናገሻ ከተማ አክሱም የገቡበት ቀን ነው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሕገ ኦሪት ተሸጋገርን ወደ ክርስቶስ መርታ የምታደርሰንን ቅድስት ኦሪትን የተቀበልን ዛሬ ነው፤ በወርቅ የተለበጠውን ጽላት ከነ ሌዋውያኑ ኦሪቱን ከነ መተርጉማኑ ተሰጠን፡፡ የብሉይ ኪዳን ድኅነት ለሁሉ መሆን አይችልምና እኛ ቅዱሳት ንዋያቱን ስንቀበል እስራኤል ባዶ ሆነች፡፡ ግብጻውያን በኃይለ እግዚአብሔር ተረትተው በኵሮቻቸውን አጡ፤ እስራኤል በሃይማኖት ድል ተነሥታ በኵሮቿን ለኢትዮጵያ ሰጠች፡፡ ከዛሬ ጀምሮ የሰሎሞን በኩር ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ ይነግሣል፡፡ እግዚአብሔር የማለላት የዳዊት ዙፋን በኋላም የእግዚአብሔር ልጅ የወረሳት የዳዊት ምንግሥት በኢትዮጵያ ተዘረጋች፡፡ መዝ 131፥11

Friday, 29 November 2019


የነፍሴ ጥያቄ ፫
በትዳር ውስጥ ተቻችሎ መኖር እንዴት ይቻላል?
በዚህ ዐምድ ሥር አስቀድሜ እንደተናገርሁት አስቀድሞ በኔ ዘንድ ያለውን የነፍሴን ጥያቄ መመለስ አስቤ የጀመርሁት ሲሆን ከእኔም በተጨማሪ የብዙ ነፍሳትን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመልስበት ዐምድ ነው፡፡
ለዛሬ ከተላኩልኝ ጥያቄዎች መካከል ይህን መረጥሁት፡፡ እግዚአብሔር በረድኤት አይለየን፡፡
አባታችን አዳም ለመጀመሪያ ጊዜ የጠየቀው ጥያቄ ቢኖር የሚረዳው ጓደኛ ለማግኘት ነው፡፡ ዓለምን እና በውስጧ ያለውን ሁሉ ያለ ንፍገት በልግስና ለሰው ልጆች አባት አዳም የሰጠው ጌታ ዘፍ 1፥28 የሚረዳው እንደ እርሱ ያለ ረዳት ሳይሰጠው ለአንድ ሱባኤ ያክል ዘግይቶበታል፡፡ ሔዋንን ለአዳም ማስገኘት ሰማይና ምድርን አሳምሮ ፈጥሮ ለአዳም ከመስጠት የሚበልጥ ሆኖ አይደለም፤ አዳም በገዛ ፈቃዱ ሔዋንን ጠይቆ ከሥላሴ ይቀበል ዘንድ ስለሚገባ ነው እንጅ፡፡
የእግዚአብሔር ዝምታ በአዳም ሕይወት ውስጥ የታየው በሔዋን ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ሳይጠይቀው አርዓያውን መልኩን ሰጥቶ ፈጠረው፣ ሳይለምነው በፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው፣ ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ስም እንዲያወጣ አሠለጠነው ዘፍ 2፥19 ነገር ግን ሔዋንን ሳይሰጠው ብቻውን አዘገየው መልአካዊ ባሕርይ ያለው ፍጥረት በመሆኑ እንደ እንስሳት ሲፈጠር ጀምሮ የሴት ጓደኛ አልተሰጠችውም እስከ ሰባተኛው ቀን መጨረሻ ድረስ ዝም ብሎታል፤ ከዚህ በኋላ ግን አዳም ለእንስሳት ስም ባወጣበት ጊዜ ሁለት፣ ሁለት ሁነው ቢያያቸው ‹‹እኔን ብቻ ያለ ረዳት ለምን ፈጠርኸኝ›› ብሎ ጠየቀ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ የተባለው ቃል ከዚህ በኋላ ነው የሚመጣው ‹‹ለአዳምሰ ኢተረክበ ሎቱ ረድኤት ዘከማሁ ንግበር ሎቱ ቢፀ ዘይረድኦ፤ ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም የሚረዳው ጓደኛ እንፍጠርለት›› ዘፍ 2፥21 የሚለውን ቃል እግዚአብሔር ተናገረ፡፡ በዚህ ቃል መሠረት በአርዓያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው ሰው እርሱን የምትመስል ሴት ከጎኑ ፈጠረለት፡፡
ገነትን ጫጉላ ቤት፣ እግዚአብሔርን አባት፣ ቅዱሳን መላእክትን እንደ ዘመድ ወዳጅ አድርገው በቅድስት ምድር በገነት ውስጥ ኖሩ፡፡
ትዳር በሰው ልጅ ፈቃድ፣ በእግዚአብሔር ፈጻሚነት የተጀመረ ሲሆን
·       በገነት ውስጥ ሆኖ
·       በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ
·       በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ተከቦ ባለበት ሰዓት ፈተና ሊያጋጥመው ይችል ይሆን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ አወ እውነት ነው የሚል ይሆናል፡፡
አዳምና ሔዋን ጠብና ክርክርን ሳያውቁ የኖሩት በሰባቱ ዓመታት ብቻ ነው ከዚያ በኋላ ኃጢአት ወደ ሰው ባሕርይ ሲገባ መለያየት ይጀምራሉ፡፡ የሞትን ዛፍ ስለመብላቱ ሲጠየቅ ‹‹ካንተ ጋር ትሁን ብለህ የሰጠኸኝ ሴት ሰጠችኝና በላሁ›› ዘፍ 3፥12 አለ፡፡ ጠብ በዚህ ጊዜ ተጀምሯል፤ ‹‹ይህች አጥንት ካጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋየ ናት እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› ዘፍ 2፥23 ብሎ ወደ ራሱ ያቀረባት፣ ስለ እርሷ እናትና አባትን ሌላውንም ሁሉ ትቶ እንደሚከተላት የተነገረላት የአዳም ምትክ (ሴት) ኃጢአትን ባወቀ ሰው ዘንድ ሞገስን አላገኘችም፡፡
በእርግጥም ከተፈጠረ ቀን ጀምሮ እሷ እስከተገኘችበት ቀን ድረስ አንቀላፋ ተብሎ ያልተነገረለት አዳም ለእሷ ሲል አንቀላፋ፣ ከአጥንቱ ተከፍላ እንደተፈጠረች ቢያውቅም ወደዳት እንጅ አልጠላትም፣ ዕራቁቱን ሆኖ ሲቀርባት የማያፍራት ዕራቁቷን ሆና ስትቀርበው የማይጠላት ባሏ አልነበረምን? ስለምን እንዲህ ያለ መከራን አመጣችበት? እሱ ሰው ለመሆን ምክንያት ቢሆናት እሷ ለመሞት ምክንያት ሆነችው፤ እሱ ወደ ገነት ቀድሞ ገብቶ አስገባት እሷ ከገነት አስወጣችው፡፡
ይህ በሆነ ጊዜ ዝም የሚል አዳም ማግኘት እንደምን ይቻላል? ኃጢአትንስ ያወቀ ሰው በደልን ሁሉ ሽሮ ሰዉን መውደድ እንዴት ይችላል? እግዚአብሔር በፈጠረው ትዳር ውስጥ እግዚአብሔር ያልፈጠራቸው ችግሮች ሲፈጠሩ እንዴት እናልፋቸዋለን? የሰው ልጅ የገነባውን ለማፍረስ ዓለምን የከከበቧት አጋንንት ብዙ ናቸው ከእነዚህ አጋንንት ዐይን የተሰወረ ትዳር ማገኘት የሚቻለው እንዴት ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በመጻሕፍት ውስጥ ያሉ ብዙ ትዳሮችን ምስክር አድርገን በቀጣይ እናያቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

Thursday, 21 November 2019

 
ጠላቶቻችን ሆይ!
በሥጋ ወንድሞቻችን በወንጌል በኩል ግን ጠላቶቻችን ከሆኑ ሰዎች ጋር ለመኖር ልምድ ያለው እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማንም በዓለም ላይ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡ አባቶቻችን ጊዜ ቢያጋጥማቸው ሥልጣን ቢደላደልላቸው እንደ መንግሥት ያስገብሩ ይሆናል እንጅ ማንንም በሃይማኖት ምክንያት በደል አያደርሱም ነበር በእርግጥ ማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅብዓ መንግሥት አክብራ የሾመችው እንደ መሆኑ ክርስቲያናዊ መንግሥት በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ የጎሣ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ክርስቲያን የመሆን አዝማሚያ ይታይባቸው ነበር ነገር ግን በራሳቸው ፈቃድ እንጅ ማንም አስገድዶ ክርስቲያን አላደረጋቸውም፡፡
ምን አልባትም በሃይማኖት ምክንያት ቁጥጥር ተደርጎ ከሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ አባ ጅፋር ባሉ አክራሪ እስላሞች የተደረገው ነው እሚሆነው፡፡ አባ ጅፋር ጅማን በሙሉ እስላም ለማድረግ ቋንቋዋንም አረበኛ ለማድረግ ይሠሩ ነበር ይባላል ያንጊዜ ዓጼ ምኒልክ ሰምተው ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደ ጻፉላቸው ጳውሎስ ኞኞ ጽፏል፡፡ የሐረር ሡልጣኖችም ከዓጼ ምኒልክ ጋር ጦርነት የመክፈታቸው ምክንያት እስላም በመሆናቸው ሳይሆን ማዕከላዊው መንግሥትም እስላም ካልሆነ አንገብርም በማለታቸው እንደሆነ ተጽፏል፡፡ እንዲያውም ግብር እንዲያስገቡ ወታደሮች ሲላኩ የእስላም ቆብና ጀለብያ ለዓጼ ምኒልክ ልከውላቸዋል ይባላል፡፡
ይህ በመሆኑ ምክንያት ካልሆነ ከጠላት ጋር ሀሳቡን አክብሮ በመኖር ከእኛ ጋር የሚተካከል ታሪክ ያለው ሰው ማነው? ከዛሬ በቀር በወንጌል ካልሆነ በሥጋ ጠላት ኖሮብን አያውቅም ነበር፤ ዛሬ ግን በወንጌል ብቻ ሳይሆን በሥጋም ጠላቶቻችን በዙ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መከራን እየተቀበሉ ነው፡፡
ሲገድሉንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከነገሥታቱ ጋር ሆና እንደ በደለቻቸው ሲናገሩ ይሰማል፤ ነገር ግን ታሪክ ባለማወቃቸው ይስታሉ እንጅ  ታሪካችን እንደዚያ አያሳይም፡፡ እስላም ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እኛኮ በመንግሥት ደረጃ ተዋቅረናል፤ የኢትዮጵያ ክርስትና እንደ ሌሎቹ ሀገራት በሕዝባዊ ቤት የተጀመረ አይደለም በነገሥታት ቤተ መንግሥት ተጀምሮ እየተስፋፋ የመጣ ነው እንጅ፡፡ ያንጊዜ ነገሥታቱ ያለ ምክረ ካህን በኢትዮጵያ ላይ እንዲቀመጡ ሚፈቅድላቸው ይመስላቸዋል? አጼ ገላውዴዎስ የፖርቹጋልን ወታደሮች አስወጥተው የሰደዷቸው እኮ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስላልፈቀዱ ነው እንጅ የቤተ መንግሥቱ መሳፍንት ጋር ተማክረው አልነበረም፡፡
አናሲሞስ ነሲቡንስ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ያደረገው ማን ነው? በወቅቱ ከዓጼ ምኒልክ የፈቃድ ደብዳቤ እንዲሰጠው እና ወደ ወለጋ ሂዶ ወንጌል እንዲሰብክ መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ አሳትሞ እንዲያሰራጭ ያደረገው ማነው? ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ፕሮቴስታንት በኢትዮጵያ መኖሩ ያጠራጥር ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ለክፉዎችም ለዳጋጎችም ነፍስን አሳልፎ መስጠትን እንጅ በክፉ ዓለም ውስጥ ከደጋጎቹ ጋር ብቻ መኖርን አታስተምርም፡፡   
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ከአባታችሁ ሰይጣን የተማራችሁትን መግደል ማስቆም ባንችልም እናንተም ሃይማኖታችንን ማስቆም አትችሉም፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ስለክርስቶስ መሞትን አባቶቻችን ሐዋርያት አስተምረውናል፤ አምኖ መሞት እንጅ ሃይማኖትን ክዶ በሕይወት መኖር በእኛ ዘንድ ሕይወት አይደለም፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! ስታሳድዱን ያንጊዜ ዝም የምንለው ከፊታችን ያለው ክርስቶስ ‹‹ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ ደስ ይበላችሁ በሰማይ ዋጋችሁ ታላቅ ነውና›› ማቴ 5፥10 እያለ ስለሚያጽናናን ነው፡፡
Ø  ጠላቶቻን ሆይ! ቤታችንን ንብረታችንን ስታቃጥሉ ዝም ያልነው ‹‹በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና ብሎ ያስተማረን መለኮታዊ ቃል ስላለን እሱ ትዝ እያለን ነው፡፡
Ø  ጠላቶቻችን ሆይ! እናንተ መንገድ ላይ ወጥታችሁ ስትዘፍኑ እኛ ኀዘን የተቀመጥነው፤ እናንተ መንገድ ለመዝጋት ስትሰለፉ እኛ ለምኅላ የቆምነው ‹‹ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና›› ስለሚል ነው፡፡ ኃጢአት ሠርቶ ከመደሰት ስለ ክርስቶስ መከራ እየተቀበሉ ማዘን ይበልጣልና፡፡   
Ø  የአብርሃም አምላክ ካራንን ልቀቁ ሲል የተሻለች ከነዓንን ለአብርሃም አዘጋጅቶ ነው፤ አትጠራጠሩ እናንተ ሣራን ለራሳችሁ ለማድረግ ስትሮጡ እግዚአብሔር አጋርን ሳይቀር ከእጃችሁ ነጥቆ ለአብርሃም ያደርጋታል፡፡
Ø  እናንት ሰነፎች ሆይ! ኢትዮጵያ እንደ ሣራ ናት፤ የነቢይ ሚስት ናትና ንጉሥ አያገባትም፡፡ ውበቷ አስክሯችሁ ደም ግባቷ አስቷችሁ ክፉ ባታደርጉ መልካም ነው፤ ኢትዮጵያ የንጉሡ ናት፡፡ በእናንተ ፊት አንገቱን የደፋው አብርሃም ካልጸለየላችሁ የማትድኑበት ወራት ይመጣልና አብዝታችሁ አትበድሉ፡፡      

Friday, 15 November 2019


ተመለሽ ተመለሽ
ዘመን ሲከፋ ባሪያ በጌታው ላይ ገረድም በእመቤቷ ላይ ይነሣሣሉ፤ ጌታ በተወለደበትም ዘመን ሰይጣን የተቆጣጠረው ቤተ መንግሥት ጌታ በተወለደባት የገሊላ አውራጃ ነበረ፡፡ ጥበብንና ምክርን ከሰይጣን እጅ ከሚቀበል ቤተ መንግሥት እውነተኛ ፍርድ የሚወጣው ለማን ነው? ለዓለም ሁሉ የሚሆነውን የምሥራች ዜና አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ የሞት ዜና ስትሰማ ለነበረች ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ የምሥራች ቢነገራት ሰይጣን ቀንቶ ቤተ መንግሥቱን ቀሰቀሶ ሊያጠፋፋ ሞከረ፡፡
መልካም ነገር የጠፋበት ባለጊዜ ምን ሊያደርግ ይችላል ብላችሁ ታስባችሁ? ይሄው እንደምታውቁት ዓለም ሳያየው ለዓለም ሁሉ ምግብ ሊሆን ከሰማይ የመጣውን መና ሊቀብረው፣ ብርሃናችንን ሳናየው ሊያጠፋው፣ ትንሣኤአችንን ሊገለው፣ አክሊላችንን መቃብር ሊያወርደው ሰይፉን ስሎ ተነሣ፡፡ ሕብስታችን ክርስቶስ በወርቅ መሶብ በእመቤታችን ላይ ሆኖ በዓለም ሁሉ ዞረ መቅረዟ ድንግል ማርያም ብርሃናችንን ተሸክማ በጨለማው ምድራችን ተመላለሰች፡፡
ብርሃናችን ክርስቶስን ተሸክማ በዓለም የዞረችው እመቤታችን ለሦሰት ዓመት ከስድስት ወር የገጠማት ፈተና እጅግ ብዙ ነው፡፡ በሽፍቶቹ ፍርሃት፣ በረሃብና በውኃ ጥማት፣ እሾኹ እንቅፋቱ በግብፅ አሸዋ መቃጠሉ ይህ ሁሉ የደረሰባት መከራ በጥቂቱ ሲታሰብ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ዓለም ያለ መከራና ደስታ ጫፍ ያለው በመሆኑ ዛሬ ‹‹ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሂድ›› ብሎ ያዘዘው መልአክ ‹‹የዚህን ሕጻን ነፍስ የሚሷት ሞተዋልና ወደ ምድረ ገሊላ ተመለሱ›› ማቴ 2፥13 ብሎ ነገራቸው፡፡
ዛሬ የመከራ ማብቂያ ቀን ነው፡፡ ምናለበት የኢትዮጵያ አምላክ ዛሬ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን የፈተና መጨረሻ ቀን ባደረገው፡፡
ከአህጉር ሁሉ የምታንሰው ያች ናዝሬት ምንኛ የታደለች ናት የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ በእርሷ ውስጥ ተወለደ ነገር ግን ሔሮድስ አለና ምን ይደረጋል! ክፉ ሰው ባለበት ከተማ የመልካም ነገር መኖር ምንጥቅም አለው!? ዝንቦች በገቡበት የሽቱ ብልቃጥ ውስጥ ያለ መልካም ሽቱ ምን ሊጠቅም!? የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ በተመላለሰባት ከተማ ሰው በግፍ ተጨፈጨፈባት ጌታ የዳኸባት ሜዳ ደም ፈሰሰባት፡፡ እናቶች ያለ ልጅ ቀሩ የሞተችው እናታቸውን ራሔልን እየጠሩ ‹‹እናታችን ራሔል ኖረሽልን ግፋችንን ባየሽልን ኖሮ!›› እያሉ በግብፅ እንደነበሩበት ዘመን ያለ እንባቸውን ወደ ሰማይ ረጩ፡፡
ኢትዮጵያ ናዝሬት ናት ሰነፍ መንግሥት ያጋጠማት ቅድስት ከተማ-ኢትዮጵያ፡፡
ጌታ ከእናቱ ጋር ያረፈባት በእግሩ የተመላለሰባት፡፡ ዛሬ ግን ደም የሞላባት የይሁዳ ጽዋዕን ትመስላለች፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻውን የሚደብቁበት አጥተው ተጨንቀዋል፤ ለመንግሥት አደራ እንዳይሰጡት አስቀድሞ ሸሸ፤ ለወታደሩ እንዳይሰጡት አልታዘዝሁም እያለ ላልታዘዘ ሞት አሳልፎ ይሰጥባቸዋል፤ መልሰው ወደ ማኽፀናቸው ያስገቧቸዋልን!?
አራሶች ወልደው መተኛት እማይችሉባት፣ ሕሙማን ከሆስፒታል ወጥተው እሚገደሉባ፣ በሃይማኖት በትምህርት ተቋማት ተጠግቶ መዳን የማይቻልባት ሆናች ዛሬ - ኢትዮጵያ፡፡
ሔሮድስ የአዳኙን እናት አሳደዳት ኢትዮጵያ እንደ ድንግል ማርያም ዓለምን የሚያድን ታሪክ ያላት የተስፋ ምድር ናት ኢትዮጵያ ስትሰደድ መድኃኒቱን ይዛ ነው፡፡ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በረሃብ እና በጦርነት መጠጊያ በሌለው ስደት እየተሰቃየች ያለችው መድኃኒት የሚሆነውን ሃይማኖት በእጇ ስለያዘችው ሰይጣን እየቀና ሲያሳድዳት ይኖራል፡፡  ስደተኞችን ታስጠጋ የነበረች ሀገር ዛሬ ለራሷ የምትጠጋት አጥታ ስትጨነቅ ምጧ ፀንቶ መገላገል ብትፈልግ እንኳን የሚያገላግላት ሀኪም ጠፍቶእንዲህ ስትንገላታ ማየት እንዴት ይከብዳል ፡፡ እንዲያው እግዚአብሔር የተሰደደችው ኢትዮጵያን ከስደት መልሶ ወደ ሀገሯ ያግባልን፡፡ 
ጌታ ሆይ የሕጻናቱን ነፍስ የሚሹት ሰዎች የሚሞቱት መቼ ነው?
ኢትዮጵያ ሆይ! ተመለሽ ተመለሽ፡፡