፫
ከእለታት በአንድ ቀን በቤተ መቅደሱ ትይዩ ቆሜ የተለመደውን
ጸሎቴን እያደረስሁ ሳለሁ ዐይኖቼ በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ላይ የተሳለው የጌታዬ ስዕለ ስቅለት ላይ አረፉ ሰዓሊው ያዩት ሁሉ በቀጥታ
ቀራንዮ ድረስ በሕሊና እንዲገሰግሱ የሚያስገድድ መልክ ሰጥቶ ስለሳለው ማንም ቢሆን ይህንን ስዕል አይቶ ከቀራንዮ በታች መቆም አይችልም
ስዕሉን አይተው እናቶች ደረታቸውን እየደቁ ያለቅሳሉ፤ እኔም አፌ ጸሎቱን እየተናገረ ሳለ ሳላስበው እንባየ መፍሰስ ጀመረ፡፡
የአይሁድ ክፋታቸው ጭካኔአቸው ቢያበሳጨኝም የጌታየ ትዕግሥቱ፣ ሲሰድቡት ዝም
ማለቱ አስገረመኝ፤ ሲያስቀይሙት አልተቀየማቸውም፣ ኃይሉ ብዙ ሲሆን ጠላቶቹን አልተበቀላቸውም፡፡ እፍኝ ከማይሞላው የአይሁድ ክፋት
ይልቅ ሰማይን የከደነው የእግዚአብሔር ምሕረት የሰውን ክፋት አስረስቶ
ሰማየ ሰማያት ያወጣል፤ የሰውን ክፋት ሳስብ ጊዜየን ከማጠፋ ታስቦ የማይዘለቀውን የጌታዬን ትዕግሥት ባወጣ ባወርድ ይሻለኛል ብየ
ልቤን መለስሁት፡፡
ነገር ግን ይሄን አስቤ ሳልጨርስ ወዲያውኑ የተለየ ሐሳብ ወደ
ልቤ ሲገባ ተሰማኝ፤ አስቤው አላውቅም፤ ዛሬ ለምን እንደመጣብኝም አላውቅም፤ ብቻ ድንገት እንባየ የማለዳዋ ፀሐይ እንደ ደረሰችበት
ጨለማ ድራሹ ሲጠፋ ከሐሳቤ ብንን አልኩኝ ፡፡
ከስዕሉ ላይ ዐይኔን ሳልነቅል ግን ለምን ይሄ ሁሉ ሆነ? ሰባኪዎቹስ ለምን ይዋሹናል? በእርግጥ
ክርስቶስ ስለሁላችንም ነው የሞተው ለምን ይሉናል? በእርግጥ የሞተው ስለሁላችንም ነው? እንዴት ሆኖ! እኛ ምን አጠፋን! ያጠፉ
አዳምና ሔዋን ናቸው፤ እነሱ እፀ በለስን በመብላታቸው ፍርዱ በሁላችንም ላይ መሆኑ ትክክል ነው? እግዚአብሔርስ ቢሆን እራሱ ፈርዶ
እራሱ ሲያድነን ገድሎ እንደማዳን አይቆጠርበትም? እያለች
ነፍሴ በታላቅ ጦርነት ተከባ አገኘኋት
ምን ላድርግ! ከዚያ በኋላ ይህ ጥያቄ እየተመላለሰ ነፍሴን ያስጨንቃት
ጀመር ሕጉ
የተሠራ ለአዳምና ለሔዋን ነበር እኛ ባልነበርንበት ለተሻረ ሕግ ትቀጣላችሁ ካለ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ መሆኑ ምኑ ላይ ነው?
እያለ ክፉ ሐሳብ ልቡናየን ያውከው ጀመር፡፡ ክፉ ሐሳብ ያለበት ክርስቲያን
ለጸሎትም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ምቹ መንፈስ የለውም፡፡ ምን ልሁን? እንዳስለመድሁ በአምላኬና በመድኃኒቴ ፊት ቆሜ ጸሎቴን እንዳላደርስ
ክፉ ሐሳቤ ገፋፍቶ ልቤን ከቤተ መቅደሱ ውጭ አቆመው፡፡ ጥያቄየ ከእኔ ጋር እስከነበረበት ድረስ እግሬ ወደ መቅደሱ ዘወትር የመግባት
ልማድ ቢኖረውም ልቤ ግን አሸንፎ እንደወጣ ቀረ ፡፡
ታዲያ እስከ መቼ እንደዚህ እቆያለሁ እያልሁ ሳወጣ ሳወርድ የአንድ
እሑድ ማለዳ ቅዳሴ እንዳለቀ ሰባኪው ድምጽ ማጉያውን ከፍቶ ማስተማር ጀመረ፡፡ የትምህርታችን ርእስ “አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል’’
የሚል ነው ብሎ አስተዋወቀንና የእለቱን ወንጌል ማስተማር ጀመረ፡፡ እኔ ግን እንዳትፈርዱብኝ ከርእሱ ውጭ አልሰማሁም፡፡ በእርግጥ ለእኔ ከዚያ
በላይ ትምህርት አያስፈልገኝም ነበር፤ እግዚአብሔር ለኔ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ ወዶ ያንን ርእስ እንዲያነሣ እንዳደረገው ሰባኪው አላወቀም
እንጅ የዚያን ቀን እግዚአብሔር ለኔ መልስ የሚሰጥበት ቀን ነበረ፡፡ ቃሉን ከዚህ በፊት ባውቀውም እንዲህ በጨነቀኝ ቀን ብዙ ጊዜ
የማውቀው ቃል ይሰወርብኛልና አላስታወስኩትም ነበር፤ ሰባኪው ሲናገረው ስሰማ ደነገጥሁ፤
ምን ሁኘ ነው አባቶችን መጠየቅ ያልቻልሁ ብየ ራሴን ወቅሼ ትምህርቱ
እንዳበቃ ወደ ቤቴ አልተመለስሁም፤ ሲጨንቀኝ እንደማደርገው ሁሉ ከቤተ ክርስቲያኑ በስተሰሜን በኩል አንድ የማውቃቸው አባት አሉኝ፤
አባ ገብረ ኢየሱስ ይባላሉ፡፡ እሳቸው ፊት ቀርቦ እንደ ተጠቀለለ የሚመለስ የጥያቄ ጥቅል የለም ፤ እንዲያውም ትምህርታቸውን ስሰማ
እቆይና የእግዚአብሔርን ፍርዱን አደንቃለሁ፤ እንዲያው ምን ብለህ ነህ ነው ጌታዬ ስንት ታናናሽ ሕይወት ያላቸውን ሰዎች በታላላቅ
ቤት ታኖራቸዋለህ እንዲህ አይነት ታላላቅ ሰዎችን ደሞ በታናናሽ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ታደርጋለህ ፍርድህ አይመረመርም እያልሁ አደንቃለሁ፡፡
ዛሬም እንዳስለመድሁት ሰይጣን በልቤ ላይ ሳላስበው የዘራብኝን
የጥያቄ መንጋ ሰብስቤ አቀረብሁላቸው ከላይ ያነሣሁትን ጥያቄ በሙሉ ስነግራቸው አባን ከሌሎች አባቶች ልዩ የሚያደርጋቸው የሰውን
ጥያቄ ሳይንቁ መቀበላቸወ ነው፤ የኔታ ገብረ ኢየሱሰ መስቀላቸውን አፋቸው ላይ አድርገው ሲሰሙኝ ከቆዩ በኋላ መልስ መስጠት ጀመሩ
እንዲህም አሉ፡-
‹‹ልጄ መጠየቅ የሚችል ልብ ስላለህ ደስ ሊልህ ይገባል እንጅ
አትፍራ፤ መላእክት
·
መኑ
ፈጠረነ?
·
እምአይቴ
መጻእነ?
·
ለሊነኑ
በበርእስነ ተፈጠርነ?
·
ወሚመ
እምካልዕ መጻዕነ?
የሚሉ አራት ጥያቄዎችን ማንሣታቸው ከዲያብሎስ አምልጠው ፈጣሪአቸውን
ለማወቅ አብቅቶአቸዋል፤ የአንድ ቀን ጥያቄ የዘለዓለም መልስን ሰጣቸው፤ እኛም ብንሆን ሳንጠይቀው የሰጠንን ሕይወት በራሳችን ኃጢአት
ብናጣም ያጣነውን የዘለዓለም ሕይወት የመለሰልን አዳም በአርባ አንድ ሱባኤ በጠየቀው ጥያቄ ነው፡፡
አየህ ልጄ! እግዚአብሔር ሰውን ብቻውን መፍጠሩ እሱን እንዲመስል
ፈልጎ ነበር፤ ብቻውን በመንግሥቱ ጸንቶ የሚኖረው አምላክ ዓለምን ሁሉ ከባሕርዩ እንዳስገኘ ሁሉ አምላኩን የመምሰል ፀጋ የተሰጠው
አዳምም ብቻውን ተፈጥሮ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ይገኝ ዘንድ ነው ብቻውን መፈጠሩ፡፡ ከመላእክት ከእንስሳትም የሚመስለው የለም፤
ከሰው በቀር ጓደኛ ሳይኖረው የተፈጠረ ማንም አልነበረምና፡፡
ነገር ግን ይህ ሁሉ ሳይሆን ሳይፈፀም አዳም በዕፀ በለስ ምክንያት
ክብሩን ሲያጣ እንደ ሳጥናኤል ብቻውን አልተቀጣም፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ብቻውን አልተቀበላትም፤ ልጆቹም የልጅ ልጆቹም ተካፈሉት
እንጅ፡፡ ይህ የሆነው ለምን መሰለህ ከመላእክት መካከል ሳጥናኤል ቢክድ ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሌሎችም መላእክት ቅድስናቸውን አላጡም
ክብራቸውን አልተነጠቁም፤ ምክንያቱም የሳጥናኤል ባሕርይ ከሚካኤል ከገብርኤል የተለየ ባይሆንም ሚካኤልና ገብርኤልን ያስገኘ ግን
ሳጥናኤል አይደለም፡፡ አዳምና ሔዋንን ስንመለከት ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው፤ ልጆቻቸው ሁሉ የእነሱን ነፍስና ሥጋ ተካፍለው ነው
ወደ ምድር የሚመጡት፡፡ ነፍስና ሥጋቸው ረከሰባቸው ባሕርያቸው አደፈባቸው እና ልጄ ያ! የደረሰብን ቅጣት በእናትና በአባታችን ምክንያት
እንጅ እግዚአብሔር የፈረደው በአዳምና በሔዋን ነው፡፡
ምንጩ መራራ የሆነ ውኃ የትኛውንም ያክል ረጅም ርቀት ቢጓዝ
በምን ሊጣፍጥ ይችላል ? ነቢዩ ኤልሳዕ ውሃውን ከምንጩ ያጣፈጠው ምሬት ከምንጩ መጥፋት ስለሚገባው አይደል? የሰው ዘር ምንጭ ነው
የተበላሸው መርገም በምንጫችን ላይ ነው የወደቀው፡፡ ስለዚህም ማንኛችንም ከእዳ ነጻ ሳንሆን ኖርን፡፡ በባንክ ዕዳ በተያዘ ቤት
ውስጥ ብትኖርና ዕዳውን ያመጣኸው ግን አንተ ባትሆን ቤቱን ከዕዳ ማውጣት ትችላለህ? እኛምኮ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ በዕዳ የተያዘ
ሥጋና ደም ወርሰን ነው ከማኽፀን ስንወጣ የኖርነው፤ እንዴት ከዕዳ ነጻ ልናደርገው እንችላለን? የምንከፍለው ጽድቅ ቢኖረን ኖር
ከፍለን እናስለቅቀው ነበር ነገር ግን አንዳች የሚከፈል አልነበረንምና የሚከፍልልን ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እንዲሁ ተይዘን ኖርን፡፡
ከዚያ ይልቅ የእግዚአብሔር ምሕረት አይበልጥምን? በእግዚአብሔር
መንግሥት ላይ ዐመጽ የተገኘበት እንደሰው ማን ነበረ? ግን እግዚአብሔር በይቅርታው ያደፈውን፣ የበደለውን የእኛን ባሕርይ ተዋሕዶ
በእኛ ዓለም በዕኛ ባሕርይ ተወለደ፡፡ ከቀጣን ቅጣት የሚበልጥ ሥጦታውን አደረገልን፤ የሰው ባሕርይ በመንግሥተ ሰማያት ከመኖር አልፎ
በጽርሐ ዓርያም ያለችውን የሥላሴን ዙፋን ወረሰ፤ ከመላእክት እንደ አንዱ ከመሆን ይልቅ ከሥላሴ እንደ አንዱ መሆንን አገኘ፤
እውነት ነው ልጄ! ባገኘን ቅጣት ምክንያት ከሁሉ በታች ተዋርደን
ነበር፤ አሁን ደግሞ ባደረገልን ቸርነት ከእኛ በላይ መዐርግ ያለው ማንም የለም፡፡ አሁንም ባሕርያችንን አዲስ ማድረግ የመጀመሪያ
ተግባሩ ነበር፤ ዋናው ችግር ባሕርያችን መቆሸሹ፣ አሮጌ መሆኑ ነበር አላልሁም? ያንን አሮጌ ሰውነታችንን በአዲስ ሰውነት ተካልን
‹‹አዲሱን ሰው ልበሱት›› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ በመጽሐፈ ኪዳንም ላይ ‹‹ዘተውህበ ለሙስና ….. ወሐደስኮ በዘኢይማስን፤ ለጥፋት
የተሰጠ ሰው አዳምን…በማይጠፋ አደስኸው›› ተብሎ ተነግሮለታል፡፡
እና የእግዚአብሔር ጥፋት የትኛው ነው? እኛኮ የስደተኛው የአዳም
ልጆች ነበርን እግዚአብሔር ለእሱ የሰጠውን ፀጋ ሁሉ ከእሱ እጅ ነጠቀው፤ ርስቱን፣ ሕይወቱን፣ ሀብቱን ሁሉን አጣ፡፡ ባለፀጋ በነበረ
ጊዜ አልተወለድንም ድሀ በነበረ ጊዜ ወለደን ድህነቱን አወረሰን፤ እስኪ መልስልኝ ካንተ እጅ የነጠቀው ነገር አለ? መጀመሪያውኑም
ቢሆን የአዳም ባለፀግነቱ ከእግዚአብሔር የተነሣ ነበርና ከእሱ ጋር ሲጣላ ደኸየ እኛ ደሞ ከእግዚአብሔር የራቀው ሰው የአዳም ልጆች
ነን እንጅ ባለፀጋ አባት አልነበረንም ቅዱስ አባትም አልነበረንም ስለዚህም ያንጊዜ በወቅቱ ለአባታችን አዳም ለእናታችንም ሔዋን
የነበራቸውን ስፍራ ሲኦልን ወረስን የነበራቸውን ሀብት ሞትን ተካፈልን፡፡
እስር ቤት ውስጥ ያለች እናት ብትወልድ ልጁስ አብሮ እስር ቤት
አይቀመጥም? ነፍስ ሳያውቅ ማን ያወጣዋል? ነገር ግን መንግሥት ከእስር ቤት ውጭ ባያኖረውም ወተቱን ፍትፍቱን ያቀርብለታል፤ እግዚአብሔርም
ምንም እንኳን ነፍስ ስላላወቅን ከእስር ቤት ባያወጣንም እንደ ወተት እንደ ፍትፍት ያሉ ጥቃቅን ፀጋዎቹን (ነቢይነትን፣ መላእክትን፣
እግዚአብሔርን በራዕይ ማየትን ኢሳ 6÷1) አልነፈገንም፤ ነፍስ ስናውቅ ግን ከእስር ተፈታን፡፡ እንዲያውም ገነትን መውረስን ከአዳም
ቀድሞ ልጆቹ ጀመሯት ሉቃ 23÷43 ያም ሆነ ይህ በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር መወለድን ስናገኝ የአባታችን የእግዚእበሔር የሆነው
ሁሉ የእኛ ሆነ፡፡
እናም ልጄ ሆይ! ያጣህበትን ዘመን እያሰብህ ስታዝን ከምትኖር
ያገኘኸውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እያሰብህ ነፍስህን ደስ አሰኛት አሉኝ፡፡
No comments:
Post a Comment