ተመለሽ ተመለሽ
ዘመን ሲከፋ ባሪያ በጌታው ላይ
ገረድም በእመቤቷ ላይ ይነሣሣሉ፤ ጌታ በተወለደበትም ዘመን ሰይጣን የተቆጣጠረው ቤተ መንግሥት ጌታ በተወለደባት የገሊላ አውራጃ
ነበረ፡፡ ጥበብንና ምክርን ከሰይጣን እጅ ከሚቀበል ቤተ መንግሥት እውነተኛ ፍርድ የሚወጣው ለማን ነው? ለዓለም ሁሉ የሚሆነውን
የምሥራች ዜና አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ የሞት ዜና ስትሰማ ለነበረች ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ የምሥራች ቢነገራት
ሰይጣን ቀንቶ ቤተ መንግሥቱን ቀሰቀሶ ሊያጠፋፋ ሞከረ፡፡
መልካም ነገር የጠፋበት ባለጊዜ
ምን ሊያደርግ ይችላል ብላችሁ ታስባችሁ? ይሄው እንደምታውቁት ዓለም ሳያየው ለዓለም ሁሉ ምግብ ሊሆን ከሰማይ የመጣውን መና ሊቀብረው፣
ብርሃናችንን ሳናየው ሊያጠፋው፣ ትንሣኤአችንን ሊገለው፣ አክሊላችንን መቃብር ሊያወርደው ሰይፉን ስሎ ተነሣ፡፡ ሕብስታችን ክርስቶስ
በወርቅ መሶብ በእመቤታችን ላይ ሆኖ በዓለም ሁሉ ዞረ መቅረዟ ድንግል ማርያም ብርሃናችንን ተሸክማ በጨለማው ምድራችን ተመላለሰች፡፡
ብርሃናችን ክርስቶስን ተሸክማ በዓለም
የዞረችው እመቤታችን ለሦሰት ዓመት ከስድስት ወር የገጠማት ፈተና እጅግ ብዙ ነው፡፡ በሽፍቶቹ ፍርሃት፣ በረሃብና በውኃ ጥማት፣
እሾኹ እንቅፋቱ በግብፅ አሸዋ መቃጠሉ ይህ ሁሉ የደረሰባት መከራ በጥቂቱ ሲታሰብ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ዓለም ያለ መከራና
ደስታ ጫፍ ያለው በመሆኑ ዛሬ ‹‹ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሂድ›› ብሎ ያዘዘው መልአክ ‹‹የዚህን ሕጻን ነፍስ የሚሷት
ሞተዋልና ወደ ምድረ ገሊላ ተመለሱ›› ማቴ 2፥13 ብሎ ነገራቸው፡፡
ዛሬ የመከራ ማብቂያ ቀን ነው፡፡
ምናለበት የኢትዮጵያ አምላክ ዛሬ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን የፈተና መጨረሻ ቀን ባደረገው፡፡
ከአህጉር ሁሉ የምታንሰው ያች ናዝሬት
ምንኛ የታደለች ናት የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ በእርሷ ውስጥ ተወለደ ነገር ግን ሔሮድስ አለና ምን ይደረጋል! ክፉ ሰው ባለበት ከተማ
የመልካም ነገር መኖር ምንጥቅም አለው!? ዝንቦች በገቡበት የሽቱ ብልቃጥ ውስጥ ያለ መልካም ሽቱ ምን ሊጠቅም!? የዓለም መድኃኒት
ክርስቶስ በተመላለሰባት ከተማ ሰው በግፍ ተጨፈጨፈባት ጌታ የዳኸባት ሜዳ ደም ፈሰሰባት፡፡ እናቶች ያለ ልጅ ቀሩ የሞተችው እናታቸውን
ራሔልን እየጠሩ ‹‹እናታችን ራሔል ኖረሽልን ግፋችንን ባየሽልን ኖሮ!›› እያሉ በግብፅ እንደነበሩበት ዘመን ያለ እንባቸውን ወደ
ሰማይ ረጩ፡፡
ኢትዮጵያ ናዝሬት ናት ሰነፍ መንግሥት
ያጋጠማት ቅድስት ከተማ-ኢትዮጵያ፡፡
ጌታ ከእናቱ ጋር ያረፈባት በእግሩ
የተመላለሰባት፡፡ ዛሬ ግን ደም የሞላባት የይሁዳ ጽዋዕን ትመስላለች፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻውን የሚደብቁበት አጥተው ተጨንቀዋል፤
ለመንግሥት አደራ እንዳይሰጡት አስቀድሞ ሸሸ፤ ለወታደሩ እንዳይሰጡት አልታዘዝሁም እያለ ላልታዘዘ ሞት አሳልፎ ይሰጥባቸዋል፤ መልሰው
ወደ ማኽፀናቸው ያስገቧቸዋልን!?
አራሶች ወልደው መተኛት እማይችሉባት፣
ሕሙማን ከሆስፒታል ወጥተው እሚገደሉባ፣ በሃይማኖት በትምህርት ተቋማት ተጠግቶ መዳን የማይቻልባት ሆናች ዛሬ - ኢትዮጵያ፡፡
ሔሮድስ የአዳኙን እናት አሳደዳት
ኢትዮጵያ እንደ ድንግል ማርያም ዓለምን የሚያድን ታሪክ ያላት የተስፋ ምድር ናት ኢትዮጵያ ስትሰደድ መድኃኒቱን ይዛ ነው፡፡ በወንበዴዎች
ፍርሃት፣ በረሃብ እና በጦርነት መጠጊያ በሌለው ስደት እየተሰቃየች ያለችው መድኃኒት የሚሆነውን ሃይማኖት በእጇ ስለያዘችው ሰይጣን
እየቀና ሲያሳድዳት ይኖራል፡፡ ስደተኞችን ታስጠጋ የነበረች ሀገር
ዛሬ ለራሷ የምትጠጋት አጥታ ስትጨነቅ ምጧ ፀንቶ መገላገል ብትፈልግ እንኳን የሚያገላግላት ሀኪም ጠፍቶእንዲህ ስትንገላታ ማየት
እንዴት ይከብዳል ፡፡ እንዲያው እግዚአብሔር የተሰደደችው ኢትዮጵያን ከስደት መልሶ ወደ ሀገሯ ያግባልን፡፡
ጌታ ሆይ የሕጻናቱን ነፍስ የሚሹት
ሰዎች የሚሞቱት መቼ ነው?
ኢትዮጵያ ሆይ! ተመለሽ ተመለሽ፡፡
No comments:
Post a Comment